ጉባዔው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ውክልና አግኝተው በእኩልነት ያሳተፈ ነው

57

ሐረር ፤ መጋቢት 7 ቀን 2014(ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባዔ አካታችና ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ውክልና አግኝተው በእኩልነት ያሳተፈ ነው ሲሉ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

የሀገሪቱን መንግስት እንዲመራ በህዝብ ይሁንታ አግኝቶ  የተመረጠው ፓርቲው በጉባዔው ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል።

የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ  ኮሚቴ አባልና የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ የፓርቲውን አንደኛ ጉባዔ አስመልክተው  ዛሬ ለጋዜጠኞች  በሰጡት መግለጫ፤ የፓርቲው አንደኛ ጉባዔ ከብዙ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ ፈተናዎች በኋላ የተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

በዋናነት  አካታች  እና ሁሉን አቀፍ ጉባዔ እንደነበር ነው  ያብራሩት።

በዚህም ከሁሉም ሀገሪቱ አካባቢዎች እና ከሁሉም ኢትዮጵያ ጫፍ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ውክልና ያገኙበት እና በእኩልነት የተሳተፉበት ነው ብለዋል።

በጉባዔው የተካሄዱት የአመራር፣ኮሚቴ እና የአስፈጻሚ ምርጫዎችምቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ፣ግልጽ፣ዴሞክራሲያዊ፣የፓርቲውን መተዳደርያ ደንብ መሰረት ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በጉባዔው የተቀመጡ የፓርቲው አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች  ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ እና እስካሁን ባለፍንባቸው መንገዶች የነበሩ ተግዳሮች የሚፈታ፣ያገኘናቸውን ስኬቶች የበለጠ የምናጠናክርበት እና ለመጪው ትውልድ ደግሞ የተሻለ ሁኔታ የምናመቻችበት ውሳኔዎች ናቸው ሲሉ አብራርተዋል።

ከመጋቢት 2/2014 ዓ.ም. ጀምሮ ለሶሰት ቀናት የተካሄደው የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባዔ የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ  የሚያስችሉ ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን በማሳለፍ  መጠናቀቁን በወቅቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም