የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጥ ያለመ የእግር ጉዞ ሊካሄድ ነው

147

አዲስ አበባ  መጋቢት 6/2014 /ኢዜአ/ በ'ዲቦራ ፋውንዴሽን' አማካኝነት የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ሕጻናት ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ የእግር ጉዞ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው።

የዲቦራ ፋውንዴሽን ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የፋውንዴሽኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሪት መና ታፈሰ እንዳሉት፣ የእግር ጉዞው ዓለም አቀፍ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ህጻናት ቀንን በማስመልከት ነው።

ቀኑም "አካታችነት መብት እንጂ ችሮታ አይደለም" በሚል መሪ ሀሳብ ይከባራል ብለዋል።

በዚሁ መሰረት የእግር ጉዞው በመጪው እሁድ መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ አበባ ያካሂዳል ብለዋል።

እንደ ዋና ስራ አስኪያጇ ገለጻ፣ ፋውንዴሽኑ በዋናነት አካታችነት የህጻናቱ መብት እንጂ ችሮታ አለመሆኑን ለማስገንዝብ ነው።

ችግሩ ያላባቸው ህጻናት በተለይም በጤናና በትምህርት መስክ እንዲካተቱ ለቤተሰብና ለማህበረሰብ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ይላሉ።

ጉዞውም ከመስቀል አደባባይ በቦሌ ዋና መንገድ እድርጎ መዳራሻውም ግሮቭ ጋርደን እንደሚሆን ገልጸዋል።

በእግር ጉዞው ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።

ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር የተወለዱ ልጆችና ወላጆቻቸው፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በእግር ጉዞው የሚሳተፉ መሆኑንም ገልጸዋል።

ዲቦራ ፋውንዴሽን በ2011 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን የአምዕሮ ዕድገት ውስንነት ያለባቸው ህጻናት  ትኩረት እንዲያገኙ የፖሊሲ ቅስቀሳ ለማድረግና በአካታችነት ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር ላይ ይገኛል።

ፋውንዴሽኑ ህጻናቱን ታሳቢ ያደረገ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነ የትምህርት ቤት እና የስነ-ጥበብ ማዕከል በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ እያስገነባ መሆኑም ታውቋል።

በቀጣይም ወራዊ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሃ ግብር ለማካሄድ ማቀዱም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም