ሴቶች ከባድ ፈተናዎችን በድል አድራጊነት በመወጣት የስኬት ባለቤት እንደሚሆኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ

80

መጋቢት 7/2014 /ኢዜአ/ ሴቶች ምቹ ሁኔታን ሳይጠብቁ ከባድ ፈተናዎችን በድል አድራጊነት የመወጣት አቅም እንዳላቸው በርካታ ማሳያዎች አሉ ሲሉ በመከላከያ  ሚኒስቴር ሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ጥሩዬ አሰፌ ተናገሩ።

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን በተለያዩ መስኮች በጀግንነታቸው የሚጠቀሱ ሴቶች፣ የአየር ሃይል ከፍተኛ መኮንኖችና ሌሎች በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት በቢሾፍቱ የኢፌዴሪ አየር ሃይል ግቢ ተከብሯል።

በሚኒስቴሩ  የሴቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል ጥሩዬ አሰፌ፤ በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸውም ሴቶች ምቹ ሁኔታን ብቻ ሳይጠብቁ ከባድ ፈተናዎችን በድል አድራጊነት በመሻገር ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ በርካታ ማሳያዎች እንዳሉም ተናግረዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ መስኮች ከመቻልም በላይ በልጠው የሚገኙ ሴቶችን እያፈራች መሆኗን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ከማጀት እስከ አደባባይ የሚደርስባቸውን ጫና ተቋቁመው የመምራትና የማስተዳደር ብቃታቸውን በጦር ሜዳና በከባድ ስራዎች ላይ ያሳዩ ብዙ ናቸው።   

በቀጣይም ሴቶች ምቹ ሁኔታን ሳይጠብቁ  በተሰማሩበት መስክ በድል አድራጊነት ሃላፊነታቸውን የመወጣት አቅማቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ዮናስ ዘውዴ፤ ኢትዮጵያ ከጥንት እስካሁንም በርካታ ጀግና ሴቶች ያፈራች አገር መሆኗን ተናግረዋል።

በመሆኑም የሴቶችን ቀን ማክበር ብቻ ሳይሆን ምንጊዜም ተገቢ ክብርና እንክብካቤ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

አትሌት ገዛኽኝ አበራ፤ የኢትዮጵያ እናቶች ለሁላችንም ጀግኖቻችን በመሆናቸው የሚገባቸውን ክብር ልንሰጣቸው ይገባል ብሏል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ፤ በኢትዮጵያ ያሉ በርካታ ጀግና ሴቶችን ምን ጊዜም ልናከብራቸውና ልናመሰግናቸው ይገባል ብሏል።

ጀግናዋ አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በበኩሏ በኢትዮጵያ ሴቶች የጀግንነት ተምሳሌቶች፣ የሰላም አርአያዎችና የአገር ባለውለታዎች መሆናቸውን ጠቅሳለች።

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ለአገር ሰላምና አንድነት ያላቸውን ሚና በማጠናከር ኢትዮጵያን ወደ ፊት ለማራመድ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቃለች።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሴቶች ቀን ዓለም አቀፍ ይዘት ኖሮት እንዲከበር በወሰነው መሰረት እ ኤ አ ከ1975 ጀምሮ ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን (ማርች 8) እስካሁንም ይከበራል።

እለቱ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለ46ኛ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ111ኛ ጊዜ ተከብሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም