በአሸባሪው የህወሃት የወደሙ መሰረተ ልማቶችና ተቋማት መልሶ ለመገንባት የቻይና መንግስት ድጋፍ ተጠየቀ

52

ባህር ዳር ኢዜአ መጋቢት 7/2014 በአማራ ክልል በአሸባሪው የህወሃት ቡድን የወደሙ መሰረተ ልማቶችና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እየተደረገ ባለው ጥረት የቻይና መንግስት የልማት ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጠየቁ።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩአን የተመራ ልኡክ ከአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ ጋር በባህር ዳር ከተማ ውይይት እያደረገ ነው።

በውይይቱ ላይ ርዕሰ መስተዳደር   ዶክተር ይልቃል ከፋለ  እንደገለፁት አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአማራ ክልል በወረራ በቆየባቸው ጊዜያት በርካታ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል፤ ዘርፏል።

አሁን ላይ የወደሙና የተዘረፉ መሰረተ ልማቶችና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የቻይና መንግስትም የቀደመውን ወዳጅነትና የልማት አጋርነት አጠናክሮ ከማስቀጠል አንፃር በመልሶ ግንባታ ስራ  የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ርዕሰ መስተዳደሩ ጠይቀዋል።

የቻይና መንግስት የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እየተደረገ ባለው ጥረት እንዲሁም እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል በኢንዱስትሪ፣ በግንባታ፣ በግብርናና ሌሎች ዘርፎች እያደረገ ያለውን የልማት ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል  ጠይቀዋል።

"የቻይና መንግስትና ህዝብ እንደ አማራ ክልልም ሆነ እንደ ኢትዮጵያ ያለው ግንኙነት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ እና በዲፕሎማሲ ብቻ ሳይሆን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ጠንካራ ነው "ብለዋል።

ቻይና ለኢትዮጵያ ስትራቴጂክ አጋር ሀገር መሆኗን ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል ።

ውይይቱ በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታና ዘላቂ ልማት ላይ ያተኮረ ሲሆን በተለያዩ ስፍራዎች ጉብኝት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም