የኢዜአን የ80ኛ ዓመት ጉዞ የሚዘክር የፎቶና ቪዲዮ አውደ ርዕይ በአዳማ ተከፈተ

62

መጋቢት 7 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዓውደ ርዕዩን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ መርቀው ከፍተውታል።

አውደ ርዕዩ ከኦሮሚያ ብሮድካስት ኔትዎርክ (ኦ.ቢ.ኤን) ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን ለሁለት ቀናት ክፍት እንደሚሆን ታውቋል።

ኢዜአ 80ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን “በአዲስ ምዕራፍ-አስተማማኝ የዜና ምንጭ” በሚል መሪ ቃል እያከበረ እንደሚገኝ ይታወቃል።

በመርሀ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ አባገዳዎች፣ የኢዜአ ባለድርሻ አካላት፣የኦቢኤን ሰራተኞችና፣ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል።

ኢዜአ ከምስረታው ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ መረጃዎችን ተደራሽ ያደረገባቸውን ስራዎች የሚያሳዩ ፎቶዎች እና ቪዲዮች ለእይታ የሚቀርቡ ሲሆን፤ ስራዎቹ ኢዜአ የሕልውናው ማስከበር ዘመቻን ጨምሮ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያከናወናቸውን ተግባራት ያካተተ ነው።

ኢዜአ ለዜና እና ዜና ነክ ስራዎች ሲጠቀምባቸው የነበሩ መሳሪያዎችና ቁሳቁሶች በአውደ-ርዕዩ ላይ ቀርበዋል።

ኢዜአ የተመሰረተበትን 80ኛ ዓመት በማስመልከት በአዲስ አበባ ባዘጋጀው መርሃ ግብር የፎቶ አውደ ርእይ መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ መገኘታቸው ይታወቃል።

በ1934 ዓ.ም የተመሰረተው ኢዜአ ዜና እና ዜና ነክ መረጃዎችን ለመገናኛ ብዙሃን በማሰራጨት የኢትዮጵያ ብቸኛው የዜና ወኪል ሆኖ እያገለገለ ይገኛል፡፡

ተቋሙ የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን እንዲሁም ከተለያዩ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሞ እየሰራ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም