የከተማ ነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የአምስት ዓመት "የከተሞች ተቋማትና መሰረተ ልማት ማስተባበሪያ መርሃ ግብር" ይፋ ሆነ

66
አዲስ አበባ ነሃሴ 28/2010 በኢትዮጵያ የከተማ ነዋሪዎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከከተሞች እድገት ጋር ለማመጣጠን "የከተሞች ተቋማትና መሰረተ ልማት ማስተባበሪያ መርሃ ግብር" ይፋ ተደርጓል። በመላ አገሪቱ ሰባት ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ይህ መርሃ ግብር ከ2011 እስከ 2015 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ለማስፈጸሚያ 860 የአሜሪካ ዶላር በጀት ተይዞለታል። የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አቶ ጃንጥራር አባይ እንዳሉት፤ የዚህ የሶስተኛውን መርሃ ግብር በትክክል ለመተግበር  አገር አቀፍና ክልላዊ የቁጥጥር ኮሚቴዎች ተቋቁመዋል። በመጀመሪያው የአካባቢ ልማት መርሃ ግብር 19 ከተሞች፣ በሁለተኛው 44 ከተሞች የታቀፉ ሲሆን በሶስተኛው የከተሞች ተቋማትና መሰረተ ልማት ማስተባበሪያ መርሃ ግብር ደግሞ 117 ከተሞች ይሳተፋሉ ብለዋል። የራሳቸው ምክር ቤት ያላቸውና የህዝብ ቁጥራቸው ከ 20 ሺህ በላይ የሆኑ ከተሞች መስፈርቱን አሟልተው ከተገኙ የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ መሆን ይችላሉም ብለዋል። አሳታፊ የመሰረተ ልማት እቅድ ማዘጋጀት፣ አቅማቸውን ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆንና ሴቶችን ተሳታፊ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጣቸው መስፈርቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል። በዚህም የክልሎቹን ስፋት መሰረት በማድረግ ነባሮችን ጨምሮ በኦሮሚያ 38፣ በአማራ 32 በደቡብ ክልል 27 ከተሞች በመርሃ ግብሩ እንዲካተቱ መደረጉን ጠቁመዋል። የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም ተከስተ በበኩላቸው ለመርሃ ግብሩ ስኬታማነት ጠንካራ የኦዲትና የቁጥጥር ስርዓት ተዘርግቷል ብለዋል። ክልሎች የከተማ አስተዳደሮችን አቅም መገንባትና የግዥና የፋይናንስ አስተዳደር ስርዓቱን በመደገፍ ለመርሃ ግብሩ ስኬት በትጋት መስራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። አፈፃፀሙን ለመከታተል በፌደራልና በክልል ደረጃ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ ከፌደራል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ ከዋና ኦዲተር መስሪያ ቤትና ከሌሎች ተቋማት የተውጣጣ የቁጥጥርና የኦዲት ኮሚቴ ተቋቁሟል ብለዋል። ከዓለም ባንክ የ 600 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ያገኘነው "ባለፉት ሁለት መርሃ ግብሮች ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ በመቻላችን ነው" ብለዋል ሚኒስትሩ።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም