አሸባሪው ህወሓት በህዝብ ላይ ዳግም የአፈናና የጭቆና ተግባሩን በመቀጠሉ ቀያችንን ጥለን ለመውጣት ተገደናል--ተፈናቃዮች

88

ሰቆጣ መጋቢት 6/2014 (ኢዜአ) -አሸባሪው ህወሓት በህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን አፈናና ጭቆና መቋቋም አቅቷቸው ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል የገቡ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች መንግስት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠየቁ።

በአማራ ክልል ሰቆጣ ከተማ ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች በህዝቡና በአካባቢው አስተዳደር እየተደረገላቸው ላለው ጊዜያዊ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።  

የኮረም ከተማ ነዋሪና ለቤተሰቦቻቸው ደህንነት ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ እናት ለኢዜአ እንደገለፁት አሸባሪው የህወሓት ቡድን አሁንም በህዝብ ላይ የከፋ በደል፣ ግፍና አፈና እየፈፀመ ነው።

ቡድኑ እየፈፀመ ያለውን ግፍና በደል መቋቋም ባለመቻላቸው ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በእግር አቆራርጠው ወደ ሰቆጣ ከተማ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ሰቆጣ ለመድረስ በእግር ጉዞ ሲያቆራርጡም ከህወሃት ታጣቂዎች ለማምለጥ ሲሉ ሁለት ቀን ያህል በበረሃ ተኝተው አስቸጋሪ ጊዜ ማሳለፋቸውን አውስተዋል።

እየደረሰባቸው ባለው ችግር ተማረው ወደ ሰቆጣ ከመጡ በኋላ ነፃነት እንደተሰማቸውና በህዝቡም መልካም አቀባበል እንደተደረገላቸው አስታውቀዋል።

ሰቆጣ ከመጡ በኋላ በመንግስት በኩል የወር ቀለብ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመው  የመጠለያ፣ የማብሰያ፣ የአልባሳትና  የቁሳቁስ  ችግር ያለባቸው በመሆኑ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል።

የአሸባሪ ቡድኑ አባላት ከብልፅግና ጋር ትሰሩ ነበር፤ እናንተ ባንዳ ናችሁ፤ በማለት ህዝብን እንደፈለጉ ለእስርና ስቃይ እየዳረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"ኮረም ላይ ያለው ህዝብ በአሁኑ ወቅት በሰው ልጅ ላይ ሊፈፀም የማይችል ስቃይ፣ እንግልትና ሞት እየተፈራረቀበት ነው" ሲሉ ገልፀዋል።

የሽብር ቡድኑ ወጣቱን በግድ ለጦርነት እንዲሰለፍ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል ።

''ኮረም ላይ ሁሉም ነገር ተዘጋግቷል'' እንኳን ሃሳብህን ልታራምድ ይቅርና ባለችህ አነስተኛ ገንዘብ  የፈለከውን ለመሸመት ምንም አማራጭ የማይገኝበት ሁኔታ ነው ያለው " ሲሉም  አሸባሪው በህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ሰቆቃ ገልጸዋል።

ሌላዋ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ  የኮረም ከተማ  ነዋሪ የሆኑ እናት በበኩላቸው በአሸባሪው የህወሓት ቡድን አባላት እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ በመሸሽ መንታ ህፃናት ልጆቻቸውን ይዘው ሰቆጣ ከተማ ከመጡ 14 ቀን እንደሆናቸው ተናግረዋል።

"የሽብር ቡድኑ አይደግፈኝም ብሎ የጠረጠረውን ማንኛውንም ሰው በማሰርና በመግረፍ ያሰቃያል፤ ከፍ ሲልም ይገድላል፤ ወጣቶችንም በግዴታ ወደ ጦርነት እንዲሰለፉ አፈና እየፈፀምባቸው ነው" ብለዋል።

የኮረም ህዝብ ያለውን እየበላ ህይወቱን እንዳይገፋ በየቀኑ ቤት ለቤት በመዞር ምግብ ለሰራዊቱ አውጡ እየተባለ የእለት ጉርሱን እንደሚነጠቅ ጠቁመዋል።

ለሰራዊቱ ምግብ ያላዋጣ ግለሰብ ባንዳ ነህ እየተባለ ድብደባና እስር እንደሚደርስበት ተናግረዋል።
ህወሓት በአለማጣ ህዝብ ላይ የአፈናና የጭቆና ተግባሩን ሊያቆም ባለመቻሉ ቀያቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ጠቁመው  ወደ ሰቆጣ ከመጡ ወዲህ ከህብረተሰቡ ጋር በሰላም እየኖሩ እንደሆነ ገልፀዋል።

''ለብልፅግና አገልግለሃል በሚል ለእስርና ድብደባ ተዳርጌ በ30 ሺህ ብር ዋስ ተለቅቂያለሁ " ያለው ደግሞ ሌላው ስሙን መግለጽ ያልፈለገው የኮረም ከተማ ነዋሪ የሆነ ወጣት ነው።


"የኮረም ወጣት  በህወሓት ታጣቂዎች ታፍኖ እየተወሰደ  በግዳጅ ለውትድርና እንዲሰለፍ እየተደረገ ነው" ያለው ወጣቱ  ህወሓት እየፈፀመ ያለውን ግፍ በመሸሽ የኮረም ወጣትና ህዝብ ቀየውን ጥሎ እየወጣ መሆኑን ጠቁሟል።

መንግስት በህዝብ ላይ ሰቆቃና እንግልትን እያደረሰ ባለው በአሸባሪው ህወሓት ላይ እርምጃ በመውሰድ አካባቢውን ከስጋት ነፃ እንዲያደርግላቸው ወጣቱ ጠይቋል።


ከኮረም ተፈናቃዮች መካከል ሌላው ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ግለሰብ በህወሓት እየደረሰባቸው ያለውን ግፍና መከራ በመሸሽ በርካታ ወጣቶች ወደ ሰቆጣ ከተማ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

"ወጣቶችን ጨምሮ ነዋሪዎች በህወሓት ታጣቂዎች እየደረሰባቸው ካለው ግፍ በመሸሽ  ከኮረም ወደ ሰቆጣ በመምጣት በህብረተሰቡ ውስጥ ተጠግተው እየኖሩ ነው” ብለዋል።

በአሸባሪው ህወሓት እየደረሰባቸው ካለው ግፍና አፈና በመሸሽ ከኮረም ወደ ሰቆጣ እየመጡ ያሉ ነዋሪዎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ ተናግረዋል።

ከኮረምና አላማጣ ከተሞችም ተፈናቅለው የሚመጡ ሰዎች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመው መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው  ጠይቀዋል። 

የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ደስታየ ጌታሁን ከዚህ ቀደም በሽብር ቡድኑ የተፈናቀሉ ከ52 ሽህ በላይ ሰዎች በሰቆጣ፣ ወለህና ፅፅቃ መጠለያ ጣቢያ እንደሚገኙ ተናግረዋል ።

ቀያቸውን ጥለው ወደ ሰቆጣ ከተማ ለመጡ ተፈናቃዮች የምግብና ሌሎች የቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

"ወደ ከተማው የመጡ አብዛኛው ተፈናቃዮች በዘመዶቻቸው ቤት ተጠልለው ይገኛሉ" ያሉት ሃላፊው ለተፈናቃዮች መጠለያ ለማዘጋጀት ቢያንስ 400 ያህል አነስተኛ ድንኳኖች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመዋል።

ለተፈናቀዮች መጠለያና ሌሎች ድጋፎችን ለማሟላት ከክልሉና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር እየተሰራ መሆኑን አመልከተዋል።

"ከኮረምና አላማጣ ቀያቸውን ለቀው ከሚመጡ ተፈናቃዮች ጋር የሽብር ቡድኑ ተላላኪዎች በመመሳሰል ሰርገው እንዳይገቡ በኬላዎች  ላይ ቁጥጥር እየተደረገ ነው" ያሉት ደግሞ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ፓሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር አዱኛ ገብሩ ናቸው።

ተፈናቃዮች ባሉባቸው መጠለያ ጣቢያዎችም የፀጥታ አካላት አስፈላጊውን ጥበቃና ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም