ለፍትሕ ሥርዓቱ መጎልብት የምርመራ ጋዜጠኝነትን በማጠናከር መሥራት ይገባል

110

መጋቢት 06 2014(ኢዜአ) የምርመራ ጋዜጠኝነትን በማጠናከር ለፍትሕ ሥርዓቱ መጎልበት መሥራት እንደሚገባ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመራሮች አመለከቱ፡፡

የምርመራ ጋዜጠኝነት አገራዊ እና ማህበረሰባዊ ጉዳት ሊያስከትሉ በሚችሉና በድብቅ በሚፈጸሙ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጥናት በማካሄድ የሚሰራ ጥልቅ ዘገባ ነው፡፡

ዘገባው ለችግሮች መፍትሔ እንዲቀመጥ ከማድረጉም በላይ ለማህበራዊ ፍትሕ፣ ለዴሞክራሲ ግንባታና ለአገር እድገት ጉልህ ሚና እንዳለው የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የምርመራ ዘገባ ከዚህም ባሻገር ለሙስናና ለሌሎች ወንጀሎች በር ከፋች የሆኑ አሰራሮችን እስከማስቀየር እንደሚደርስም ይነገራል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ፍርድ ቤቶች የቆሙለትን እውነተኛና ሚዛናዊ ፍትህ በመስጠት ሂደት ላይ መገናኛ ብዙኃን የሚሰሯቸው የምርመራ ዘገባዎች ከፍተኛ ሚና አላቸው።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ብረሃነመስቀል ወጋሪ በፍርድ ቤቶች ለችሎት ከሚቀርቡ የወንጀል ጉዳዮች መካከል የሙስና ወንጀል ዋነኛው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ከዚህ አኳያ የምርመራ ጋዜጠኝነት መጠናከር ሙስናን እንዲሁም በድብቅ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለማጋለጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ የፍትህ ሥርዓቱ እንዲጎለብት ያግዛል ሲሉም አመልክተው የመገናኛ ብዙኃን ጠንካራ የምርመራ ዘገባ እንዲሰሩ ማበረታታትና መደገፍ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት  ተናኜ ጥላሁን በበኩላቸው፤ የተደበቁ በደሎችን ፈልፍሎ ለማጋለጥና የወንጀል ሂደቱ በመረጃና ማስረጃ ላይ ተመስርቶ ትክክለኛውን ፍርድ እንዲሰጥ የምርመራ ጋዜጠኝነት የማይተካ ሚና እንዳለው አንስተዋል፡፡

የምርመራ ጋዜጠኝነት በየቢሮው የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን፣ ጾታዊ ትንኮሳና ጥቃቶችን በማጋለጥ ለዴሞክራሲና ፍትህ መጎልበት ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለውም ነው የገለጹት።

መንግስት የምርመራ ጋዜጠኝነትን በማጠናከር የተጀመረው የፀረ-ሙስና ትግል ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም