በአገሪቱ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆናቸው ተገለፀ

97
አዳማ ነሃሴ 28/2010 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በመላ አገሪቱ የሚገኙ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። የበጀት ዓመቱን የዘርፉን ሴክተር ተቋማት የሥራ አፈፃፀም ግምገማና የ2011 ዓ.ም የመነሻ እቅድ የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምረዋል። የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ የአለም ፀጋዬ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት በበጀት ዓመት የሴቶችን ተሳትፎና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት ተመዝግቧል። በዚህም በገጠርና በከተማ ከ2 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል። ከእነዚሁ ሴቶች መካከል ከ2 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት በጥቃቅንና አነስተኛ፣ በራስ አገዝ የሥራና የሙያ አማራጮችን ጨምሮ በህብረት ሥራ ማህበራት ዘርፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። በተመሳሳይ ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑት በገጠር የግብርና ሥራ የተሰማሩ መሆናቸውን የገለፁት ሚኒስትሯ የእርሻና የግጦሽ መሬት ተጠቃሚነት መብት እንዲኖራቸው ለማስቻል በተደረገው ጥረት በበጀት ዓመቱ ከ796 ሺህ በላይ የሚሆኑት እማወራዎች የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ የሴቶች ተሳትፎና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንፃር ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ድረስ በተሰሩት የንቅናቄና ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች 13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሴቶች በቁጠባ እንዲሳተፉ ከማድረጉም ባሻገር ከ3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ ቁጠባ መሰብሰብ መቻሉን አስረድተዋል። በተለያዩ የሥራ አማራጮች ለተሰማሩ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሴቶች በአጭርና በረዥም ጊዜ የሚከፈል ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ ከመንግስትና ከተለያዩ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብድር በማመቻቸት አገልግሎቱን ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል። በበጀት ዓመቱ የተሻለ አፈፃፀም የታየ ቢሆንም የሴቶችን የግብርና ኤክስቴሽን አገልግሎት ተጠቃሚነትን ከማሳደግ አኳያ ክፍተት መኖሩን የገለፁት ደግሞ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስትራቴጅካዊ ሥራ አመራር ዳይሬክተር ወይዘሪት አዜብ ረዘነ ናቸው። የግብዓት አቅርቦት እጥረት፣ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ቴክኖሎጅ አቅርቦት ችግር፣ ለምርታቸው በቂ የገበያ ትስስር አለመኖር፣ በብድርና ቁጠባ ላይ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ መሆን በእቅድ አፈጻፀም ውስጥ የተለዩ ክፍተቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የመድረኩ ዓላማም በበጀት ዓመቱ በሥራ አፈጻፀም ውስጥ የታዩ ቁልፍ ችግሮችን በመለየት ከዘርፉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር ለተሻለ ውጤትና ለውጥ የጋራ የማስፈፀሚያ ስልትና አቅጣጫ ለማስቀመጥና ለተፈፃሚነቱ ለመረባረብ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው መድረክ ላይ ከፌዴራልና ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ተቋማት፣ ከሴቶች አደረጃጀቶችና ማህበራት የተወጣጡ አመራሮችና የሥራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም