የሳንሱሲ-ቡራዩ-ታጠቅ ኬላ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት 94 በመቶ ተጠናቋል

97

አዲስ አበባ መጋቢት 06/2014(ኢዜአ) ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የሳንሱሲ-ቡራዩ-ታጠቅ ኬላ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ገለጸ።

በባለሥልጣኑ የፕሮጀክቱ ተጠሪ መሃንዲስ አቶ ስንታየሁ አየለ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ በ2009 ዓ.ም ቢጀመርም በተለያዩ ምክንያቶች በተያዘለት የጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ አልተቻለም።

በተለይም ከወሰን ማስከበርና የካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ የነበሩ ችግሮች ለፕሮጀክቱ መጓተት መንስኤ እንደነበሩ ገልጸው አሁን ላይ በኅብረተሰቡ ትብብር ፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ በ739 ሚሊዮን ብር በጀት የተጀመረው ይኸው ፕሮጀክት አሁን ላይ 94 በመቶ መድረሱን ጠቁመው እስካሁን 820 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ነው የገለጹት።

ቀደም ሲል በነበረውን የፕሮጀክቱ ዲዛይን ላይ ማሻሻያ ተደርጎበት በአዲስ መልኩ መገንባቱንና አንዳንድ ተጨማሪ ሥራዎች ማካተቱ ለበጀቱ ጭማሪ በምክንያትነት አንስተዋል።  

መንገዱ በገጠር 22 ሜትር በከተሞች ደግሞ 32 ሜትር ስፋት እንዳለው ጠቁመው የመንገዱ አጠቃላይ ርዝመትም 13 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ነው ብለዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቱ አምቦን ነቀምትን ጌዶን አሶሳን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍሎች የሚደረገውን የትራንስፖርት አገልግሎት ያሳልጠዋል ብለዋል።  

ፕሮጀክቱ ከዋናው ከተማ ጋር የሚያገናኝ በመሆኑ የትራንስፖርት ፍሰቱን ከዚሀ ቀደም ከነበረው የተሻለ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።

የቡራዩ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈሪ ንጋቱ በበኩላቸው የመንገዱ መገንባት የሳንሱሲ፣ ከታ፤ ቡራዩ፣ ድሬ፣ ገፈርሳና ኬላ የመሳሰሉ ከተሞችን እድገት ያፋጥናል ብለዋል።

ይህም የከተሞቹን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ በአዎንታዊ መልኩ ይደግፋል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም