በቤላ ተራራ ጥብቅ ደን የተከሰተውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው

173

ሰቆጣ፤ መጋቢት 6/2014 (ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በጋዝጊብላ ወረዳ ቤላ ተራራ ላይ የተከሰተው የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ።


በብሄረሰብ አስተዳደሩ ትልቁ ተራራ እንደሆነ የሚነገርለት የቤላ ተራራ ከመጋቢት 3/2014 ዓ.ም. ረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ  ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ የእሳት አደጋው እንደተነሳ ተመልክቷል።

በተራራው ላይ የተነሳው የእሳት አደጋ እሰካሁን  150 ሄክታር ጥብቅ ደን ማውደሙን  የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ሲሳይ አዳነ ለኢዜአ ገልጸዋል።

እሳት ለማጥፋት የጋዝጊብላ ወረዳ ወጣቶችን ጨምሮ ሌሎችም ነዋሪዎችና  የፀጥታ አካላት  ባደረጉት ርብርብ የሰደድ እሳቱን መስፋፋት እንደተገደበ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በባህላዊ መንገድ  እሳቱን ለማጥፋት ባደረገው ጥረትም በአሁኑ ወቅት በአስ ከተማ በኩል የተነሳው እሳት ሙሉ በሙሉ ማጥፋት መቻሉን ጠቁመዋል።

በተራራው በሌላኛው በኩል ያለውን እሳት ለማጥፋት የተቀናጀ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል።

በተራራው ዙሪያ በሚገኙ አምስት ቀበሌዎች ባለው ጥብቅ ደን በርካታ ወጣቶችና አርሶ አደሮች በማር ምርት የተሰማሩበት መሆኑን ጠቅሰዋል።

እሳቱ በአፋጣኝ መቆጣጠር  ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ የዞኑን ጨምሮ በአማራ ክልል የሚመለከታቸው  ተቋማት  እገዛ እንደሚያስፈልጋቸውም አቶ ሲሳይ አመልክተዋል።


የቤላ ተራራ ጥብቅ ደን ከ953 ሄክታር በላይ የሚሸፍን ሲሆን፣ በውስጡም ጥቁር እንጭት፣ ጽድ ፣ኮሶ፣ ወይራና መሰል የእፅዋት ዝርያዎች እንዲሁም የተለያዩ የዱር እንስሳት እንዳለው ከጽህፈት ቤቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም