በብልጽግና ፓርቲ ቅድመ ጉባኤ ግምገማ 2 ሺህ 574 አመራሮች ከሃላፊነት እንዲነሱ ተደርጓል

70

አዲስ አበባ መጋቢት 06/2014(ኢዜአ) በብልጽግና ፓርቲ ቅድመ ጉባኤ ግምገማ 2 ሺህ 574 አመራሮች ከኃላፊነት እንዲነሱ መደረጉን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

በፓርቲው አንደኛ ጉባኤ የተመዘገቡ ስኬቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመገምገም የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍና አቅጣጫዎችንም በማስቀመጥ በስኬት መጠናቀቁ ተገልጿል።

ከቅድመ ጉባኤ እስከ ፍፃሜው ድረስ የነበረውን ክንውን በማስመልከት የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በቅድመ ጉባኤ ግምገማ 108 ሺህ 258 አመራሮች ተገምግመው በ10 ሺህ 658 አመራሮች ላይ የተለያየ ደረጃ ያለው እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

በፓርቲው እርምጃ ከተወሰደባቸው 10 ሺህ 658 አመራሮች መካከል 2 ሺህ 574ቱ ከኃላፊነት እንዲነሱ መደረጉንም ተናግረዋል።

በቀሪዎቹ  ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል ማስጠንቀቂያ፣ ከደረጃ ዝቅ ማድረግና የቦታ ሽግሽግ መደረጉን ጠቅሰዋል።

አመራሮች የተገመገሙባቸው መስፈርቶች የሙያ ስነ-ምግባር፣ አገልግሎት የመስጠት፣ የሥራ ውጤታማነትና ሌሎችም የብቃት መለኪያዎች መሆናቸውንም አብራርተዋል።

በጉባኤውም ፓርቲው በህዝቡ የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የሚያስችል ግምገማ ተደርጎ ውሳኔ ተላልፏል ብለዋል።

በጉባኤው ከለውጥ ወዲህ ያጋጠሙ አገራዊ ስኬቶችና ውጤቶች በጥልቀት መገምገማቸውንም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

በፖለቲካው ዘርፍ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋት ሥራዎች፣ አሳሪ ህጎችን ማሻሻል፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ነፃና ገለልተኛ እንዲሆኑ በማድረግ ጥሩ ውጤት መመዝገቡንም ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያ ቅቡልነት ያለው መንግስት መመስረት እንዲቻል ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ መካሄዱም በስኬት ተነስቷል ብለዋል።

የአገር ሉዓላዊነትንና የግዛት አንድነትን በማስከበርም ፓርቲው ጠንካራ አመራር መስጠት መቻሉም እንዲሁ።

በኢኮኖሚ ዘርፍም ከልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም አንፃር የነበረው ውስንነት ተገምግሞ በጥራት፣ በፍጥነት፣ ባልተጋነነ ወጪ ፕሮጀክቶች እንዲከናወኑ ማድረግ የሚያስችል አቅጣጫ መቀመጡንም ገልጸዋል።

የግብርና ዘርፉን የማዘመንና ምርትና ማርታማነትን ለማሳደግ የተሰራው ሥራ እንዲሁ በስኬታማነት መታየቱን ገልጸዋል።

በማሕበራዊ ልማት ዘርፍም የሕዝቦችን አብሮነት የሚያጠናከሩ ተግባራት መከናወናቸውንና የሃይማኖት አባቶችን ጭምር ማቀራረብ መቻሉ በበጎ መልኩ መታየቱንም አንስተዋል።

በሌላ በኩል በጉባኤው ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መንስኤና መፍትሔም በጥልቀት መገምገሙን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት በተለይም የሰላምና ደህንነት ጉዳይ ትልቅ ፈተና የነበረ መሆኑም በጉባኤው በስፋት ተነስቷል ነው ያሉት።

የውስጥና የውጭ ኃይሎች ጥምረት በፈጠሩት ጦርነት የሰው ህይወት ማለፉ፣ አካል መጉደሉንና የንብረት ውድመት መከሰቱ ተነስቷል ብለዋል።

ከዚህም ባለፈ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራሮች ተግዳሮት ሆነው እንደቆዩም ገልጸዋል።

በጉባኤው አገራዊ ለውጡን ማስቀጠል፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ማጠናከር፣ የአገርን አንድነትና የህዝብን ሰላም ማስጠበቅ፣ የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት መጠበቅና ሌሎችም የቀጣይ ዋነኛ ትኩረቱ አድርጓቸዋል።

የፓርቲ ዲሲፕሊንን በማክበር ውስጣዊ አንድነት ማጠናከር፣ ሕዝቡን ማሳተፍ፣ አገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠርና በጦርነት የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ማቋቋምም ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ ተቀምጧል።

የብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ "ከፈተና ወደ ልዕልና" በሚል መሪ ሃሳብ ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም መካሄዱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም