በሚኤሶ ከተማ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮባንድ ዕቃ በቁጥጥር ስር ዋለ

105

ጭሮ ፤ መጋቢት 06/2014 (ኢዜአ) ግምቱ ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የኮንትሮባንድ ዕቃ በሚኤሶ ከተማ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የኮንትሮባንድ ዕቃው በቁጥጥር ስር የዋለው መጋቢት 4 ቀን 2014ዓ.ም የሰሌዳ ቁጥር በሌላቸው ሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎች ሲጓጓዝ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በተደረገ ፍተሻ መሆኑን  የሚኤሶ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጅን አህመዲን ከድር ገልጸዋል።

ከውጭ የገባውና በምስራቅ ኢትዮጵያ  በኩል ወደ መሀል ሀገር ለማሳለፍ ሲሞከር በቁጥጥር ስር  የዋለው የኮንትሮባንድ ዕቃው ሚኤሶ ከተማ እንደደረስ መቆጣጠር መቻሉን አስታውቀዋል።

በዚህም ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው  የተለያዩ አልባሳት፤ ሲጋራና ሺሻ መገኘቱን አስረድተዋል።

ኤፍ ኤስ አር  እና አይሱዙ የሆኑት የጭነት ተሽከርካሪዎቹ ሾፌሮች ለጊዜው ከአካባቢው ሸሽተው ቢያመልጡም ለመያዝ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑን ዋና ሳጅን አህመዲን ተናግረዋል፡፡

ህገወጥ ንግድ የህዝብና የመንግስትን ሀብት የሚያቀጭጭ፤ ሰላምና ፀጥታንም የሚያደፈርስ በመሆኑ ጥቆማ በመስጠት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም