የከተማ አስተዳደሩ 110 የከተማ አውቶቡሶችን ወደ አገር ቤት ለማስገባትና የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማዘመን የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ

121

መጋቢት 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 110 ዘመናዊ የከተማ አውቶቡሶችን ወደ አገር ቤት ለማስገባትና የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማዘመን ከሁለት የቻይና ኩባንያዎች ጋር ስምምነት ተፈራረመ።

በስምምነቱ መሰረት ዘመናዊ የከተማ አውቶቡሶቹን የሚያቀርበው ''ዩቶንግ ባስ ካምፓኒ'' የተባለ የቻይና ኩባንያ ሲሆን የአይ.ሲቲ መሰረተ ልማቱን የሚከውነው ደግሞ ''ሼንዶ ሂሰንስ ትራንስ ቴክ '' የተሰኘ የቻይና ኩባንያ መሆኑ ታውቋል።

የከተማዋ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዚሁ ወቅት በመዲናዋ በትራንስፖርቱ ዘርፍ እየተስተዋለ ያለውን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ አማራጮች እየተወሰዱ መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም መንግስት አገልግሎቱን ለማዘመን ባለፈው ሳምንት ከ1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን የመንገድ ፕሮጀክትን ማስመረቁን አንስተዋል።

የከተማዋ የትራንስፖርት ችግር ረዥም ጊዜ ያስቆጠረና ውሰብስብ መሆኑን በመገንዘብ ችግሩን ለማቃለል የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

በስምምነቱ መሰረትም ከዓለም ባንክ ከተገኘ 30 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ውስጥ ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ ተጨማሪ ዘመናዊ የከተማ አውቶብሶች ወደ አገር ቤት እንደሚገቡ ገልጸዋል።

አውቶቡሶቹ በ8 ወር ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ወደ አገር ቤት ገብተው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ከ14 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዲሁም ከአገር ውስጥ ተጨማሪ 9 ሚሊዮን ብር በጀት በመያዝ የትራንስፖርት አገልሎቱን ለማዘመን እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በመዲናዋ አገልግሎት በመስጠት ላይ ለሚገኙት አንበሳ የከተማ አውቶብሶች የደህንነት ካሜራን ጨምሮ ሌሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች እንደሚገጠሙላቸው አብራርተዋል፡፡

ይህም በመዲናዋ እየተስፋፋ የመጣውን ስርቆትና ሌሎች ወንጀሎችን ለመከላከል ሚናው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አውቶብሶቹ ከወረቀት የጸዳና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል፡፡

አውቶብሶቹ በተቀመጠላቸው አግባብ መሰረት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ለመቆጣጠር እንደሚያግዝም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም