ከ300 በላይ የበሽታ አይነቶች ላይ የተደረጉ ጥናቶችን የያዘ የጤና አትላስ ይፋ ሆነ

206

አዲስ አበባ፣  መጋቢት  5/2014 /ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ከ300 በላይ የበሽታ አይነቶች ላይ በአምስት አመታት ውስጥ የተደረጉ ጥናቶችን የያዘ የጤና አትላስ ይፋ ሆነ።

የጤና አትላሱ እ.ኤ.አ. ከ1990 እስከ 2019 በኢትዮጵያ በሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተከሰቱ በሽታዎችን እና የበሽታዎቹን ሥርጭት የሚያሳይ ጥናት የያዘ መሆኑም ታውቋል።

በአትላሱ የጥናት ግኝቶች ሞትና ልደት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች፣ የትምህርት ደረጃ እንዲሁም ለሞት መንስኤ የሆኑ የበሽታ አይነቶች ተካተዋል።

ጥናቱን የመሩት የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ መረጃ ማደራጃ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር አወቀ ምስጋናው፤ ለጤና እክል አጋላጭ መንስኤዎች፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና አማካይ የሰዎች መኖሪያ ዕድሜን በተመለከተም በአትላሱ ከተቀመጡ መረጃዎች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አምስት ዓመታት የፈጀውን ጥናት የጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና ሌሎች አጋር አካላት በጋራ ማከናወናቸውንም ገልጸዋል።

እንደ ዶክተር አወቀ ገለፃ በአትላሱ ኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት ያለፈችበትን የጤና ሥርዓት ጠንካራና ደካማ ጎን ለይቶ አስቀምጧል።

የጤና ሚኒስቴርና የክልል ጤና ቢሮዎች የተለያዩ ውሳኔዎችን በሚያሳልፉበት ወቅትና ምርምርን መሰረት ያደረጉ ሥራዎችን ሲሰሩ አትላሱ በእጅጉ ያግዛልም ነው ያሉት።

በጥናቱ ከ800 በላይ ተመራማሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ከ300 በላይ የበሽታ አይነቶች ተካተውበታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ በሆነው አትላስ ከ1 ሺህ በላይ መረጃዎችን ከተለያዩ ተቋማት በመሰብሰብ የተሰራ የትንተና ውጤት መሆኑንም ተናግረዋል።

በከተሞች ያለውን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም በክልሎች መካከል ያለውን የጤና አገልግሎት በተመለከተም በአትላሱ በስፋት ተካቷል።

በኢትዮጵያ አማካይ የዜጎች ዕድሜ ጣሪያ እ.ኤ.አ. በ1980 ዓ.ም ከነበረበት 45 ዓመት በ2019 ወደ 69 ዓመት ከፍ እንዳለ በጥናቱ ተመልክቷል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ የጤና መረጃ ሳምንት ተብሎ በታወጀው መሰረት የዘንድሮው የጤና ሳምንት በተያዘው ሳምንት በመከበር ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም