የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ያማረ ሐሳብ ይዘን በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል

63

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 05/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ያማረ ሐሳብ ይዘን በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አሳሰቡ።

በ895 ሚሊየን ብር የተገነባው የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት ህንጻ የፓርቲው ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንቶች እንዲሁም ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል።

የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልእክት የበለጸገችና ያማረች አገር ለመገንባት የአመራሩ ሚና ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ለፓርቲው ዋና ጽህፈት ቤት የተገነባው ቢሮ ያማረ መሆኑን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ ገዢ ሐሳብ ይዘን በትጋት መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።

የፖርቲው ዋና ጽህፈት ቤት ህንጻ በባለሃብቶች፣ በፓርቲው አባላት እና ሌሎች አካላት ተሳትፎ በመገንባቱ አመስግነው የተሻለና አዲስ አስተሳሰብ በመላበስ አገር ለመገንባትና ህዝብ ለማገልገል ዝግጁ መሆን ይገባል ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፤ የህንጻው ግንባታ 895 ሚሊየን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን የተለያዩ አገልግሎቶች ያሉበት ዘመናዊ ቢሮ መሆኑን ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ሥፍራ፣ የመኪና ማቆሚያ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የእንግዳ ማረፊያ፣ ቤተ-መፃህፍትን ጨምሮ ልዩ ልዩ ክፍሎች እንዳሉት ዘርዝረዋል።

የፖርቲው ጽህፈት ቤት የአረንጓዴ ሥፍራውን ጨምሮ አጠቃላይ 7 ሺህ 860 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን 4 ሺህ 700 ካሬ ሜትር ደግሞ ህንጻው ያረፈበት ሥፍራ መሆኑን አስረድተዋል።

ብልጽግና የዘመናዊ ቢሮ ባለቤት በመሆኑም ለአመራሩና አባላቱ እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ላለፉት ሦስት ቀናት በአዲስ አበባ ባካሄደው አንደኛ ጉባኤ በአገራዊ፣ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር በማድረግ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም