በሐረሪ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዝ የምግብ ዘይትና የስንዴ ዱቄት ለህብረተሰቡ ሊከፋፈል ነው

66

ሐረር ፤ መጋቢት 5 ቀን 2014 (ኢዜአ) ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዝ 54 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይትና 2 ሺህ ኩንታል የስንዴ ዱቄት ከነገ ጀምሮ ለህብረተሰቡ እንደሚከፋፈል የሐረሪ ክልል የንግድ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።


ጽህፈት ቤቱ በክልሉ  ዘይትን ጨምሮ ሌሎችንም የፍጆታ ምርቶችን  ያለአግባብ  በመጋዘን የሚያከማቹ  ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ኮሚቴ አቋቁሞ  ወደ ስራ መግባቱንም ገልጿል።

በክልሉ ገበያን ለማረጋጋት  በመንግስት ድጎማ የመጣው የምግብ ዘይትና  የስንዴ ዱቄቱ ከነገ ጀምሮ ለተጠቃሚው ለማከፋፈል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ቡሽራ አልይ ተናግረዋል።

በክልሉ በሚገኙ ገጠር እና ከተማ በሚገኙ ዩኒየኖች አማካኝነት ለሸማቾች ማህበር በማከፋፈል ለህብረተሰቡ እንዲዳረስ ይደረጋል ብለዋል።

በዚህም አንድ ሊትር 93 ብር ከ50 ሳንቲም፣አምስት ሊትር  በ462 ብር እና 20 ሊትር ደግሞ በ1ሺህ 848 ብር  እንዲሁም አንድ ኪሎ ስንዴ ዱቄት በ39 ብር ከ50 ሳንቲም ዋጋ እንደሚከፋፈል ይፋ አድርገዋል።

ዘይቱና ዱቄቱ ለህብረተሰቡ በተገቢው ተደራሽ እንዲሆን   ከወረዳ አመራር ጋር በመሆን ጥብቅ የቁጥጥር ስራ እንደሚከናወን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት 35ሺ 928 ሊትር ዘይት እንደደረሳቸው የተናገሩት ደግሞ  የሐረር ሁለገብ ሸማቾች ዩኒየን የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሚስጥር በላቸው ናቸው።

ለዩኑየኑ የቀረበውን ዘይት በተተመነው ዋጋ መሰረት ለማህበራት በማከፋፈል ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በፍትሃዊነት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

በክልሉ ባለፈው ሳምንት በህገ ወጥ መንገድ የተገኘው የምግብ ዘይት በቁጥጥር ስር ውሎ በተመጣጣኝ ዋጋ  ለህብረተሰቡ እንዲከፋፈል መደረጉን የክልል  የንግድ ልማት ጽህፈት ቤት አስታውሷል።

ባለፉት አራት ወራት በመንግስት ድጎማ 250 ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት ቀርቦ ለክልሉ ህብረተሰቡ መከፋፈሉም ተመልክቷል።

ከዚህ ሌላ ጽህፈት ቤቱ በክልሉ ዘይትን ጨምሮ ሌሎችንም የፍጆታ ምርቶችን በመጋዘን ውስጥ የሚያከማቹ  ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ኮሚቴ አቋቁሞ እየተሰራ እንደሚገኝም ተገልጿል።

በመሰል ህገ ወጥ ተግባር ላይ  የተሰማሩ አካላት  ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም  ጽህፈት ቤቱ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም