ማህበሩ ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነትን ለማሳደግ ለሚከናወኑ ተግባራት የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል

72

አዲስ አበባ መጋቢት  5/2014 /ኢዜአ /የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነት ለማሳደግ ለሚከናወኑ ተግባራት የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት የጤና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር 33ኛ ዓመታዊ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ሲሆን፤ ጉባኤው ችግርን የሚቋቋም ጠንካራ የጤና ስርዓት መገንባት ላይ ትኩረቱን አድርጓል።  

ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ጉባኤ የጤና ሚኒስትር አማካሪ ዶክተር ከበደ ወርቁ፣የአሜሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ተወካይና የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡   

በጉባኤው በኢትዮጵያ ጤና ስርዓት የሚስተዋሉ ክፍተቶች፣መፍትሄ መንገዶች ላይ የሚያተኩሩ 50 ጥናታዊ ጹሁፎች እንደሚቀርቡም ይጠበቃል።   

ዶክተር ከበደ ወርቁ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ማህበሩ በጤና ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ዝግጅትና ግምገማዎች ላይ በንቃት እየታሳተፈ ይገኛል፡፡

ማህበሩ ለጤና አገልግሎት ጥራት መሻሻል የሚያግዙ የምርምር ስራዎች  በመሳተፍ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ይህንን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

መንግስት ሁሉን አቀፍ የጤና ሽፋን ተደራሽነት ለማሳደግ በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ ማህበሩ የበኩሉን ድጋፍ  ማድረግ እንደሚጠበቅበትም እንዲሁ፡፡

በተለይም የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን ተደራሽነት ለማስፋት የሚያደርግውን እንቅስቃሴ ውጤታማ እንዲሆን በማገዝ አለበት ነው ያሉት፡፡  

የማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶክተር ምትኬ ሞላ በበኩላቸው ጉባኤው አሁን ጤና ተቋማት ወቅታዊ ሁኔታውን እንዴት እየተቋቋሙት ነው እንዲሁም እንዴት በቅንጅት መስራት ይቻላል የሚለውን በሰፊው ይዳስሳል ብለዋል፡፡  

በጉባኤው ከሚደረጉ ወይይቶችና ከሚቀርቡ የጥናት ውጤቶች የተጨመቁ ሀሳቦች ለፖሊሲ ግብዓት እንደሚያገለግሉም አብራርተዋል።  

እንደ ዶክተር ምትኬ ገለጻ፤ ማህበሩ እስካሁን ባለው ሂደት የጤና ዘርፉን በሰው ኃይልና በአደረጃጀት ማሻሻል የሚያስችሉ ጥናቶችን አቅርቧል።

በዘርፉ የሚሰሩ ባለሙያዎች ያከናወኗቸው የጥናትና ምርምር ስራዎች ታትመው ለአገልግሎት እንዲበቁ የራሱን ጥረት እያደረገ መሆኑንም አክለዋል።      

በጉባኤው መክፈቻ ሥነ-ስርዓት ላይ በህብረተሰብ ጤና ምርምርና አገልግሎት ዘርፍ የተሻለ ተግባር ላከናወኑ ወጣትና አንጋፋ ባለሙያዎች ሽልማት ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ማህበር ከ8 ሺህ 800 በላይ የተመዘገቡ አባላት እንዳሉት ከማህበሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።      

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም