የዴሞክራሲ ልምምዳችን ኢትዮጵያን የሚያጸና እንጂ በአገርና ህዝብ ላይ አደጋ የሚጥል ሊሆን አይገባም

73

የዴሞክራሲ ልምምዳችን ኢትዮጵያን የሚያጸና እንጂ በአገርና ህዝብ ላይ አደጋ የሚጥል ሊሆን አይገባም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከብልጽግና ፓርቲ አንደኛ ጉባኤ ተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ለኢትዮጵያ ብልጽግና እውን መሆን ሰላም ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም የብልጽግና ፓርቲ በቀጣይ ለህግ የበላይነት መከበርና ሰላም መስፈን ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ነው ያሉት፡፡

በኢትዮጵያ የሚነሱ የትኛውም አይነት ጉዳዮች በሰላም ሊፈቱ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰላም የምንፈልገው የትኛውንም አካል ለማስደሰት ሳይሆን የኢትዮጵያን ብልጽግና ስለምንሻ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የዴሞክራሲ ልምምዳችን ኢትዮጵያን የሚያጸና እንጂ በአገርና ህዝብ ላይ አደጋ የሚጥል ሊሆን አይገባም ነው ያሉት፡፡

"የኢትዮጵያ ብልጽግና አይቀሬ ነው" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ብልጽግና ለመሄድ በምናደርገው ጥረት የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በድል ለመሻገር መዘጋጀት አለብን ብለዋል።

በተለይ ሌብነትን መታገል የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ገበያ ከተከሰተው የዋጋ መናር ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ እየተፈጠረ ያለውን የኑሮ ውድነት ችግር ለማቃለል በበጋ ስንዴ ልማት የተጀመረውን ጥረት ጨምሮ ሌሎች የልማት ስራዎችም ገቢራዊ እንደሚሆኑም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት 25 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ እንደምታገኝ ጠቁመው፤ ይህን ማጠናከር ከተቻለ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ በቀጣይ ጥቂት ዓመታት የስንዴ ምርት ወደ ውጭ አገር ትልካለች ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም