በኢፈ ቦሩ ፕሮጀክት በተገነቡ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እያገኙ ነው

108

መጋቢት 04/2014(ኢዜአ) ... በ"ኢፈ ቦሩ" ፕሮጀክት በአቅራቢያቸው የተገነቡ ትምህርት ቤቶች ያጋጥሟቸው የነበሩ ችግሮችን ከማቃለላቸውም በላይ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲያገኙ እንዳስቻሏቸው የቱሉ ሀርቡ፣ ኩዩና ሳዳሞ ኢፈ ቦሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ገለጹ።

በፕሮጀክቱ የተገነቡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በክልሉም ሆነ በሀገሪቱ ለሚገነቡ መሰል የትምህርት ቤቶች ግንባታ ደረጃ መነሻ ተሞክሮ መሆን እንደሚችሉ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ ገልጿል።

የሆለታ ቱሉ ሀርቡ፣ የገልገል ኩዩና የሳዳሞ ወልመራ ኢፈ ቦሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በትምህርት ቤቶቹ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት እያገኙ ነው።

እንደ ተማሪዎቹ ገለጻ  በ"ኢፈ ቦሩ" ፕሮጀክት በአቅራቢያቸው የተገነቡ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲማሩና ነገን ተስፋ አድርገው እንዲያልሙ እድርገዋቸዋል።

የሆለታ ቱሉ ሀርቡ ኢፈ ቦሩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪ ዓለምነህ ተረፈ እንዳለው ትምህርት ቤቱ ቀደም ሲል ትምሀርት ለማግኘት ከሁለት እስከ ሶስት ሰዓት ያደርጉት የነበረውን የእግር ጉዞ አስቀረቷል።

እንዲሁም በረጅም የእግር ጉዞ ይደርስባቸው የነበረውን ድካምና እንግልት በማስቀረት በአቅራቢያቸው ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ተረጋግተው እንዲማሩና ሰፊ የማንበቢያ ጊዜ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ተናግሯል።

ሌላዋ የትምህርት ቤቱ 9ኛ ክፍል ተማሪ ወርቄ ደቻሳ እንዳለችው የትምህርት ቤቶቹ በአቅራቢያቸው መገንባት በተለይ "ሴት ተማሪዎች ያጋጥማቸው የነበረውን ችግር እንዲቀንስ ከማድረጉም በላይ ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ማግኘት አስችሏቸዋል"።

በኢፈ ቦሩ ሳዳሞ ወልመራ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሲፈን ኤባም በበኩሏ የትምህርት ቤቶቹ መገንባት ቀደም ሲል አነስተኛ የነበረውን  የሴቶች የ2ኛ ደረጃ የትምህርት ተሳትፎ እንዲጨምር ማስቻሉን ገልጻለች።

የኢፈ ቦሩ ገልገል ኩዩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ9ኛ ክፍል ተማሪ አያንቱ ታከለ በበኩሏ ደረጃውን በጠበቀ ትምህርት ቤት በመማሯ ደስተኛ መሆኗን ገልጻ፤  በዚህ ደረጃ መማራቸው ለወደፊት ስኬታቸው ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግራለች።

የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ በበኩሉ በፕሮጀክት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሀገሪቱ ጭምር ለሚገነቡ መሰል የትምህርት ቤቶች ግንባታ ደረጃ መነሻ ተሞክሮ መሆን እንደሚችሉ ገልጿል።

በምክትል ቢሮ ሀላፊ ደረጃ  የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ አማካሪ አቶ ኤፍሬም ተሰማ እንደገለጹት የክልሉ መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና ተደራሽነትን ለማሳደግ በ”ኢፈ ቦሩ” ፕሮጀክት በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ደረጃቸውን የጠበቁ 100 ትምህርት ቤቶች አስገንብቶ ስራ አስጀምሯል።

አማካሪው እንዳሉት ትምህርት ቢሮው በ2010 ዓ.ም ባካሄደው የትምህርት ቤቶች ደረጃ ጥናት በክልሉ ከሚገኙ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 91 በመቶ የሚሆኑት የሚጠበቀውን መስፈርት ያላሟሉና ከደረጃ በታች መሆናቸውን አረጋግጧል።

ከደረጃ በታች የነበሩትን ትምህርት ቤቶች በአንዴ ደረጃቸውን የጠበቁ ማድረግ ስለማይቻል ቢሮው የተለያዩ የትምህርት ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።

ኢፈ ቦሩ  ፕሮጀክት ሁለት ዓላማዎችን ያነገበ ሲሆን፤ በፕሮጀክቱ የተገነቡት ትምህርት ቤቶች ለመሰል የትምህርት ቤቶች ግንባታ ጥሩ የተሞክሮ መቅሰሚያ መሆን እንደሚችሉም ተናግረዋል። 

በክልሉ በሚገኙ  ዞኖችና ከተሞች ያሉ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ተጠንቶና ተደራሽነትን ያማከሉ ሆነው መገንባታቸው ደግሞ ሁለተኛው ዓላማው ነው ብለዋል።

አብሮ ማደግን እንደ ዓላማ ይዞ የተነሳው የክልሉ መንግሥት ከኦሮሚያ ውጭ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ፣ በሶማሌና አፋር ክልሎችም መሰል የኢፈ ቦሩ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት ላይ መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም