ጉባኤው ፍጹም ነጻና አሳታፊ በመሆን ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ እድገት መሰረት የጣለ ነው

71

መጋቢት 4/2014/ኢዜአ/ የብልጽግና ፓርቲ 1ኛ ጉባኤ ፍጹም ነጻና አሳታፊ በመሆን ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ እድገት መሰረት የጣለ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የጉባኤው ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ 1ኛ ጉባኤ በመካሄድ ላይ ሲሆን ጉባኤው ትናንት ባካሄደው ውሎ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብና ፕሮግራም እንዲሁም የፓርቲውን ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንቶች መርጧል፡፡

በተጨማሪ ጉባኤው የፓርቲውን የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም የቁጥጥርና ኤንስፔክሽን ኮሚሽን ሪፖርት አድምጦ አጽድቋል፡፡

በእነዚህ ሁሉ ሂደቶች የጉባኤው ተሳታፊዎች ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሃሳባቸውን በመግለጽ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ነው ለኢዜአ የተናገሩት፡፡

ጉባኤው ከሁሉም የኢትዮጲያ አካባቢዎች የመጡ የፓርቲው አባላት እንደ ቀድሞው የኢህአዴግ ዘመን የዳር ተመልካች ሳይሆኑ እኩል ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ከብልጽግና ፓርቲ ሐረሪ ቅርንጫፍ የመጡትና የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ነቢል መኸዲ፤ በጉባኤው ቀድሞ አጋር ተብለው ተመልካች ብቻ የነበሩ ፓርቲዎች አሁን ላይ በአገራቸው ጉዳይ እኩል ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጉባኤው ፍጹም ዴሞክራሲያዊ የሆነና አሳታፊ ምህዳር የተፈጠረበት መሆኑን ጠቅሰው ይህም ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እድገት ጠንካራ መሰረት የሚጥል ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ከብልጽግና ፓርቲ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ቅርንጫፍ የመጡትና የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አበራሽ ደቻስ፤ በጉባኤው ላይ የታየው አሳታፊነት የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ግንባታና ብልጽግና እውን እንደሚሆን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ጉባኤው ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የእድገት ጎዳና ለማሻገር የሚረዱ ውሳኔዎች የተላለፉበት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ዳግማዊት ሞገስ ናቸው፡፡

ይህም ለቀጣይ የልማት ስራዎች መሰረት የሚጥል መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በብልጽግና ፓርቲ የቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጀማል ረዲ በበኩላቸው ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ያለ ልዩነት እኩል እየተሳተፉ በመሆናቸው ጉባኤውን ከዚህ ቀደም ከተከናወኑ የገዢ ፓርቲ ጉባኤዎች ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የጉባኤው ተሳታፊዎችም ፍጹም ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ሃሳባቸውን በነጻነት እያነጸባረቁ ስለመሆናቸው ነው የተናገሩት፡፡

የብልጽግና ፓርቲ 1ኛ ጉባኤ የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ በዛሬው እለት እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም