የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተጠቅመን ካለማነው ማሳ የተሻለ ምርት እንጠብቃለን - የኢሉአባቦር ዞን አርሶ አደሮች

56
መቱ ነሃሴ 28/2010 በዘንድሮው የመኸር ወቅት የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተጠቅመው ካለሙት ማሳ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ በኢሉአባቦር ዞን አስተያየታቸውን የሰጡ የመቱ፣ ሁሩሙና ቢሎ ኖጳ ወረዳ አርሶአደሮች ገለጹ፡፡ በዞኑ በዘንድሮው የመኸር ወቅት እስካሁን ከ134ሺ ሄክታር በላይ መሬት በተለያየ የሰብል ዘር ተሸፍኗል፡፡ በሁሩሙ ወረዳ ቶማ ዮምቢ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ወንድሙ ተክሌ በሰጡት አስተያየት ሁለት ሄክታር የሚሆን ማሳቸውን በበቆሎ፣ ማሽላና ጤፍ ዘር ሸፍነው እያለሙ ነው፡፡ ከማሳቸው ውስጥ ከአንድ ሄክታር በላይ የሚሆነውን  ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ተጠቅመው በቆሎ በመስመር መዝራታቸውን ተናግረዋል፡፡ ባለፈው አመት ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በአግባቡ ሳይጠቀሙ በብተና ካለሙት አንድ ሄክታር የበቆሎ ማሳ ከ20 ኩንታል ያልበለጠ ምርት እንደሰበሰቡ ተናግረዋል፡፡ በዚህ አመት ግን የተሟላ ፓኬጅ ከመጠቀም ባለፈ ለምርት ጥበቃና እንክብካቤ የበለጠ ትኩረት በመስጠታቸው ምርታማነታቸው በእጥፍ ያድጋል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ከአንድ ሄክታር ተኩል በላይ በሚሆን ማሳቸው ላይ ከበቆሎ በተጨማሪ  አተርና  ጤፍ ሙሉ በመስመር ዘርተው እያለሙ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በቢሎ ኖጳ ወረዳ ቃሮ ማረሚ ቀበሌ አርሶ አደር ታሪኩ ዲባባ ናቸው፡፡ ሙሉ ፖኬጅ ተጠቅመው ካለሙት ማሳም ባለፈው ዓመት በባህላዊ መንገድ በብተና ካለሙት ማሳ ብልጫ ያለው ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ በዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ አዲሱ ማሙሻ እንዳሉት በ2010/2011 የምርት ዘመን ከ200ሺ በላይ አርሶአደሮችን በልማቱ በማሳተፍ እስካሁን ከ134ሺ ሄክታር በላይ መሬት በዘር ተሸፍኗል፡፡ በዞኑ 13 ወረዳዎች በአገዳ፣ ብርዕ፣ ቅባት ሰብሎች ዘር የተሸፈነው መሬት በምርት ዘመኑ ለማልማት ከታቀደው 140ሺ ሄክታር በላይ መሬት ውስጥ ነው፡፡ አርሶአደሮቹ በዘር ከሸፈኑት መሬት ውስጥ ከ18ሺ400 ሄክታር በላይ የሚሆነውን ምርጥ ዘር ፣ግብአትና የመስመር ቴክኖሎጂ በመጠቀም በተሟላ ፓኬጅ ማልማታቸውን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን በዘር ያልተሸፈነው መሬትም እስከ ቀጣዩ ሳምንት ፈጥነው በሚደርስ የሰብልና የጥራጥሬ ዘር እንደሚሸፈን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ እየተካሄደ ካለው የመኸር እርሻ በመልማት ላይ ካለው መሬት ከ5 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም