ቻይና ከአፍሪካ ጋር በትብብር የምትሰራባቸውን መስኮች ይፋ አደረገች

62
ነሐሴ 28/2010 ቻይና ከአፍሪካ ጋር በትብብር የምትሰራባቸውን መስኮች ይፋ አደረገች፡፡ የቻይና አፍሪካ ትብብር ጉባኤ ዛሬ ተጀምሯል፡፡ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ ጉባዔውን ሲከፍቱ ይፋ እንዳደረጉት ቻይና በቀጣዮች ሶስት ዓመታት በኢንዱስትሪ፣ ኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ መሰረተልማት፣ ጤና፣ ባህል፣ አካባቢ ጥበቃና ደህንነት ዘርፎች ከአፍሪካ ሀገራት ጋር በትብብር ትሰራለች፡፡ የቻይና አፍሪካ ምጣኔ ሀብታዊና የንግድ ትርኢት እንደሚመሰረትም ነው ይፋ ያደረጉት፡፡ ሀገራቸው የአፍሪካ ሀገራት እኤአ ከ2030 በፊት የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ ያስቀመጡትን ግብ እንደምትደግፍ ገልጸው  በድርቅ ምክንያት ጉዳት ለሚደርስባቸው የአፍሪካ ሀገራት ከ146 ሚሊዮን ዶላር በላይ የአስቸኳይ ጊዜ ሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡ በኃይል፣ ትራንስፖርትና ቴሌኮምዩኒኬሽን መስኮች ያለውን ትብብር በማጠናከር የአህጉሪቱን መሰረተልማት ግንባታ እንደምትደግፍም ነው ፕሬዝዳንቱ ያረጋገጡት፡፡ ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት ቻይና ከአህጉሪቱ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነት ለማሳለጥ የሚያግዙ 50 ፕሮጀክቶችንና ከአካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ጋር በተያያዘ ደግሞ 50 የእርዳታ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ታደርጋለች፡፡ ሀገራቸው ለአፍሪካ ወጣቶች የሙያና መሰል ስልጠናዎችን በመስጠት የአህጉሪቱን  ማህበራዊ ልማት መደገፏን እንደምትቀጥልም  በንግግራቸው አጽንኦት ሰጥተውታል፡፡ በተመሳሳይ ከሰላምና ደህንነት ጋር በተያያዘ የቻይና አፍሪካ ፈንድን የማቋቋም እቅድት እንዳላትም ይፋ አድርገዋል፡፡ ቻይና  አህጉሪቱ በየዘርፉ ለምታከናውናቸው ተግባራት በእርዳታና  ኢንቨስትመንት  60 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ እንደምታደርግም ነው የተናገሩት፡፡ “አፍሪካን እናከብራለን፤ እንወዳለን፤ እንደግፋለን” ያሉት ፕሬዝዳንት ሺ የቻይና እና አፍሪካ ህዝቦችን  የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ትብብሮችን አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል፡፡ ለሁለት ቀናት የሚካሔደው ጉባዔ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ የሌሎች አፍሪካ ሀገራት መሪዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም