አገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የኃይማኖት አባቶች አዎንታዊ አስተዋጽዖ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል

60

መጋቢት 01 / 2014( ኢዜአ ) አገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የኃይማኖት አባቶች አዎንታዊ አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አሳሰበ።

የአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ''በውይይት እሴት ባህል ግንባታ የኃይማኖት ተቋማት አስተዋጽዖ'' በሚል መሪ ኃሳብ ውይይት ተደርጓል።

የአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሃፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ የኃይማኖት አባቶች ሚና ከፍተኛ ነው።

በኢትዮጵያ ሲንከባለሉ የመጡ የቅራኔ ምክንያቶች እልባት እንዲያገኙ አገራዊ ምክክር ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው የኃይማኖት አባቶች ንቁ ተሳታፊ መሆን አለባቸው ብለዋል።

በአገራዊ ምክክሩ ላይ የኃይማኖት አባቶች በጎ ኃሳቦችን በማቅረብና በእምነት ተቋማቸው ያለውን የውይይት እሴት ይበልጥ በመጠቀም ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ገልጸዋል።    

የኃይማኖት አባቶች ተሰሚነታቸውን በመጠቀም አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን መስራት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ተወካይ መምህር የማነብርሃን አከለ ናቸው።

አርሳቸውም እንደ አንድ የኃይማኖት አባት የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው የኃይማኖት አባቶች አገራዊ ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ከሚያደርጓቸው ተሳትፎ ጎን ለጎን በጸሎትም ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

 ''የኃይማኖት አባቶች ለሕዝቡ ቅርብ በመሆናቸውና ተሰሚነታቸው ከፍ ያለ በመሆኑ  ውይይቱ ፍሬያማ እንዲሆን ያስችለዋል'' ያሉት ደግሞ ከእስልምና ኃይማኖት  ሐጂ ነስሩ ሰኢድ ናቸው።

በመሆኑም በውይቱ የኃይማኖት አባቶች በሳል ኃሳቦችን በመሥጠት በአገሪቷ እንደ ችግር ሲነሱ የቆዩ ችግሮችን እልባት እንዲያገኙ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

ከኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ እየሱስን ቄስ ለማ ሶቦቃ፤ የእምነት መሪዎች እንደ አገር የገጠሙ ችግሮች መፍትሄ እንዲያገኙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በመሆኑም የኃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው አገራዊ ምክክር ስኬታማ እንዲሆን በቅንጅት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸው ለዚህም የራሳቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

በዚህም የታለመውን ዘላቂ አገራዊ ሰላምና አንድነት ለማምጣት እንደሚረዳ በመጠቆም።

በኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ 11 ኮሚሽነሮች ተሰይመውለት ሁሉን አቀፍና አሳታፊ ምክክር ለማድረግ በሂደት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም