በኢትዮጵያ የድርቅ አደጋ የሚያስከትለውን ከፍተኛ ጉዳት ለመከላከል የመስኖና የውሃ ልማት ስራን በልዩ ትኩረት መስራት ይገባል

96

አዲስ አበባ መጋቢት 01/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ የድርቅ አደጋ የሚያስከትለውን ከፍተኛ ጉዳት ለመከላከል የመስኖና የውሃ ልማት ስራን በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የአየር ንብረት መዛባት፣ የሙቀት መጨመር፣ የዝናብ መዛባትና እጥረት፣ ድርቅና የጎርፍ አደጋዎች በአየር ንብረት ለውጥ ከሚከሰቱ ችገሮች መካከል ይጠቀሳሉ።

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩትና የዴንማርኩ ኮፐንሀገን ዩኒቨርሲቲ ዴቨሎፕመንታል ኢኮኖሚክስ ጥናት ክፍል በአየር ንብረት መዛባትና አቅም ግንባታ ላይ እኤአ ከ2019 እስከ 2024 የሚቆይ ጥናት እያካሄደ ነው።

የጥናቱ የመጀመሪያ ሂደት በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በደቡብ፣ በጋምቤላ ክልሎች እና በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር እየተካሄደ ይገኛል።

በኢንስቲትዩት የግብርና ገጠር ልማት ፖሊሲ ጥናት ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ታደሰ ኩማ፤ በኢትዮጵያ የድርቅ አደጋ የሚያስከትለውን ከፍተኛ ጉዳት ለመከላከል የመስኖና የውሃ ልማት ስራን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥን ተከትሎ በሰዎችና እንስሳት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትለውን ይህንን አደጋ ለመመከት ልዩ ትኩረት ያሻልም ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ በተለይም የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰበት መሆኑን ጠቁመዋል።

በምስራቅና በደቡብ የአገሪቱ አካባቢዎች በድርቁ የተነሳ ለችግር የተዳረጉ ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እንስሳት እየሞቱ መሆኑንም አስተባባሪው ተናግረዋል።

በተለይ በዚህ ዓመት በኦሮሚያና በሱማሌ ክልሎች የተከሰተውና ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ የሚገኘው ድርቅ ከአየር ንብረት መዛባት ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል።

"ቦረና ላይ ቀደም ብለን ጥሩ መኖና በቂ ውሃ ብናዘጋጅ ኖሮ ህዝቦቻችንን ለተወሰነ ጊዜ ከችግር መታደግ እንችል ነበር ሲሉ" ተናግረዋል።

በመሆኑም ድርቅን በዘላቂነት ለመቋቋም በመሰኖ ልማት ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ነው ያሉት።

በቆላማ ቦታዎች በመስኖ ልማት ላይ የሚሳተፉ ባለሀብቶችን ማበረታታት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ በእንስሳት መኖና በውሃ ልማት ላይ በትኩረት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል ።

ለዚህ ስኬት ደግሞ የመንግስት ጥረት ብቻውን በቂ ባለመሆኑ የግል ባሀብቶች በስፋት እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል።

ከኮፐንሀገን ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር ፒተር ፊስከር፤ ተለዋዋጭ የሆነው የአየር ንብረት መዛባት በግብርና ምርት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የሜካናይዜሽን አስተራረስ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በግብርና ምርት ላይ መሻሻሎች ቢኖሩም የአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛው ተግዳሮት መሆኑን ገለጸዋል።

ይህንን ለመቋቋም በመስኖ ልማትና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ላይ በስፋት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም