አሸባሪው ህወሓት በዋግ ኽምራ ላፈናቀላቸው ወገኖች ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

88

ሰቆጣ ፤መጋቢት 1/2014(ኢዜአ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ላፈናቀላቸው ወገኖች ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ።

የአማራ ልማት ማህበር(አልማ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መላኩ ፋንታ፤ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በወራሪው ቡድን  ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በሰቆጣ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ወገኖችን ተመልክተዋል።

አቶ መላኩ ፤ አሸባሪው በፈጸመው ወረራ ከሞቀ ቤታቸው የተፈናቀሉ እናቶች፣ አባቶችና ህፃናት በከባድ የህይወት ፈተና ውስጥ እንደሚገኙ መመልከታቸውን ተናግረዋል።

በሌሎች አካባቢዎችም በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በችግር ውስጥ ቢሆኑም፤ በሰቆጣ መጠለያ ጣቢያ ያሉት ግን  በከፋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መረዳታቸውን ገልጸዋል።

ማህበሩ ከዋግ ልማት ማህበር በጋራ በመሆን ረጂ ድርጅቶችን በማስተባበር በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ለመደገፍ የድርሻውን እንደሚወጣ  ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል።

ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች ያሉባቸውን ችግር ለማቃለል ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የግሎባል አሊያንስ በኢትዮጵያ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ አምሃ መኮንን በበኩላቸው፤ በጦርነቱ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው በሰቆጣ መጠለያ በከፋ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችን ለመርዳት በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር ሚናቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ምክትል አስተዳዳሪ  አቶ ሹመት ጥላሁን እንዳመለከቱት፤ በወረራ ከ50 ሺህ በላይ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው በሰቆጣና ፅፅቃ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ።

የተፈናቃዮችን ችግር ለማቃለል በመንግሥትና በአንዳንድ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም፤ከችግሩ ስፋት አንፃር በቂ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

ሁሉም ወገን ለተፈናቃዮቹ ተገቢውን ድጋፍ እንዲደረግላቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ግሎባል አሊያንስ  ሰሞኑን በዋግ ኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ከቤት ንብረታቸው 

ለተፈናቀሉ ወገኖች የ5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ፣ አልባሳትና የፍራሽ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም