ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የሚኖራትን ተሰሚነት ከፍ ለማድረግ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከላትን ማጠናከር ይገባል

81

መጋቢት 01 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የሚኖራትን ተሰሚነት ከፍ ለማድረግ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከላትን ማጠናከር እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ክንውኖች ላይ በማተኮር ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ የሚኖራትን ተሰሚነት ከፍ ለማድረግ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ማዕከላትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ይሄንኑ በመረዳት የአርባ ምንጭ፣ ሀዋሳ፣ ቦንጋ፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች የከፈቷቸውን ማእከላት ለአብነት ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ አቅም ለማጎልበት ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም እነዚህን ማዕከላት አቋቁመው ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የአረብ ሊግ አገራት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን እንደማይጎዳ ግንዛቤ እንዲይዙ ለማድረግ ለሊባኖሱ መሪ ማብራሪያ መሰጠቱን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

በሊባኖስ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሊባኖስ መሪን በማግኘት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን እንደማይጎዳ አስረድተዋል ብለዋል።

ይህም ሊባኖስ የአረብ ሊግ አባል በመሆኗ በአረብ ሊግ የተያዘውን የተሳሳተ አቋም ለማስረዳት ያግዛል ነው ያሉት።

በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተፈጠረው ግጭት የዓለም ስጋን መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያም በጥንቃቄ ትመለከተዋለች ብለዋል።

በአገራቱ ጉዳይ ላይ በተባበሩት መንግስታት ስብሰባ በተሰጠው ድምጽ ላይ ኢትዮጵያ በቦታው ያልተገኘችው ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ስለምትሻ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም