ጽህፈት ቤቱ ከ206 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች መያዙን አስታወቀ

65

ዲላ፤ መጋቢት 1/2014 (ኢዜአ) በጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከ206 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።

ጽህፈት ቤቱ የኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን መከላከል  በሚቻልበት ዙሪያ ከጸጥታና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የጋራ የምክክር መድረክ  በዲላ ከተማ አካሂዷል።

በዚህ ወቅት የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ሜሪድ በወቅቱ እንደገለጹት፤  የኮንትሮባንድ ንግድ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ጫና ከማሳደሩ ባለፈ የጸረ ሰላም  ሃይሎች የሀብት ምንጭ እየሆነ መጥቷል።

በደቡብ ኢትዮጵያ የሚካሄዱ የኮንትሮባንድ ዝውውሮችን ለመቆጣጠር ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም  የሚፈለገው ውጤት አልተገኝም ብለዋል።

በተለይ አደንዛዥ ዕፅ፣ የኤሌክትሮንክስ ቁሳቁሶች ፣  ልባሽ ጨርቅ፣ጫማ፣የመድሃኒትና የተሽከርካሪ መለዋወጫ ዕቃዎች ጎልተው የሚታዩ ኮንትሮባንድ ዝውውሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ባለፉት ስድስት ወራትም ድርጊቱን ለመግታት በተደረገ ጥረት  206 ሚሊዮን 700 ሺህ ብር የሚገመቱ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች  መቆጣጠር  መቻሉን አስታውቀዋል።

የኤሌክትሮንክስ ቁሳቁሶች ፣ ልባሽ ጨርቅ፣ጫማና መድሃኒት በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

እነዚህ ዕቃዎች መቆጣጠር የተቻለው በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስር በሚገኙ ሻሸመኔ ፣ ጪጩ፣ ያቤሎ፣ ሞያሌን ጨምሮ በስምንት  መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች አማካኝነት በተደረገ ብርበራና ፍተሻ መሆኑን አስረድተዋል።

የኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድን በዘላቂነት ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የተቀናጀ ስራ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አቶ ታደሰ አመልክተዋል።

''የኮንትሮባንድና ህገ ወጥ ንግድ በሀገርና ህዝብ ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው'' ያሉት ደግሞ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አለማየሁ ማሞ ናቸው።

የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በዓይነትም በመጠንም እየጨመረ ከመምጣቱ ባለፈ ስልቱ ተለዋዋጭና ውስብስብ እየሆነ መምጣቱን ጠቅሰው፤ ይህን መከላከል የሚችል የፖሊስ ቁመና እንዲኖር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በተለይ በቁጥጥር ስር የዋሉ ኮንትሮባንድ አዘዋዋሪዎች ላይ በቂ ምርመራ በማድረግ በኩል ውስንነቶችና በገንዘብ ዋስትና ወንጀለኞችን የመፍታት የህግ አሰራር መኖሩ በስራቸው ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን ጠቁመው፤  ሊሻሻል እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ህገወጦችን መከላከል በጸጥታ አካላትና በጉምሩክ ሰራተኞች አቅም ብቻ የሚሸፈን ባለመሆኑ ህብረተሰቡ የችግሩን አሰከፊነትን በመረዳት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም መልዕክት አሰተላልፋል።

በጉምሩክ ኮሚሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የጪጩ መቆጣጠሪያ ጣቢያ ሃላፊ ኮማንደር መስቀሌ አራጋው በበኩላቸው፤ የህብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስ፣  የባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶና ተናቦ አለመስራት ህገወጥ ድርጊቱን ለመቆጣጠር ችግር መሆኑን ተናግረዋል።

ሆኖም በረቀቀ መንገድና በጉምሩክ ተቆጣጣሪዎች የስነ ምግባር ችግር  የሚያልፉ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን  ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም