ከጉባኤው ሊካሄድ ለታሰበው ሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ውሳኔ ይጠበቃል- ምሁራን

76

ሶዶ የካቲት 30/2014 (ኢዜአ) የብልጽግና ፓርቲ ከሚያካሂደው መደበኛ ጉባኤ ሊካሄድ ለታሰበው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ስኬታማነት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ውሳኔ ይጠበቃል ሲሉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አመለከቱ።

ኢዜአ መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓም የሚካሄደውን የፓርቲውን መደበኛ ጉባኤ በማስመልከት ከዩኒቨርሲቲው ምሁራን ጋር ቃለ ምልልስ አካሂዷል።

የዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ዋና ዲን ተወካይ አቶ ታመነ ኤና እንዳሉት የብልጽግና ፓርቲ በሚያካሂደው ጉባኤ በሀገሪቱ ወቅታዊ  የፓለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ የሚያሳልፈው ውሳኔ ለሀገራዊ ምክክር መድረኩ ስኬታማነት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር እንደሚሆን ይጠበቃል ።

ሀገራዊ ምክክር መድረኩ ሁሉን አካታች እንደመሆኑ የተለያዩ ብዥታዎችን ማጥራት እንደሚገባ ጠቁመው  ፓርቲው በጉባኤው የሚያሳልፈው ውሳኔ ብዥታዎችን ለማጥራት ቁልፍ ሚና የሚጫወት ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል ።
አንድ ሆኖ ወደፊት መጓዝ ከተፈለገ ከኋላ ያሉ ችግሮችን በማከም ዳግም የችግሩ ተጎጂ ላለመሆን የማጥራት ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

"ጉባኤው የሚያሳልፈው ውሳኔ ችግሮች እንዳይደገሙ ድንበር ከማበጀት አኳያ ፖለቲካዊ ቁርሾዎችን ለማከም አስተዋፅኦ ይኖረዋል"  ሲሉ አክለዋል።
እንደ አቶ ታመነ ገለጻ ፓርቲው ለሀገራዊ የምክክር መድረኩ በሀሳብ ልዕልናና በዴሞክራሲ ስርዓት የሚያምን የፖለቲካ ስርዓት ከመዘርጋት አንፃር የሚኖረው አቋም የምክክር መድረኩ ፍትሃዊና አሳታፊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ ይረዳል።

በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የፀጥታ ችግር ካለመቋጨቱ ጋር ተያይዞ ለሀገራዊ ምክክር መድረኩ ስጋት እንዳይሆን ተወያይቶ አቅጣጫ ማስቀመጥ ከፓርቲው ጉባኤ የሚጠበቅ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የስነ ዜጋና ስነምግባር ትምህርት ክፍል መምህር ጳውሎስ ወርቁ ናቸው።

አያይዘውም ከጉባኤው  ከዋጋ ግሽበቱ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳያመሩ እልባት ለመስጠት የሚረዱ ውሳኔዎች እንደሚጠበቁ አመላክተዋል ።

ሀገራዊ የምክክር መድረክ በመፍጠር ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቁርሾዎችን የፈቱ በርካታ ሀገራት መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ጳውሎስ የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ መካሄድ ሊካሄድ ለታሰበው ብሄራዊ ምክክር መድረክ ውጤታማነት  ምቹ መደላድል የሚጥል መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም