ብልጽግና በአገር ጉዳይ የዳር ተመልካች የነበረውን የፖለቲካ ስርአት በመቀየር ሁሉንም አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ስርዓት ይዞ የመጣ ፓርቲ ነው

104

አዲስ አባባ የካቲት 30/2014 /ኢዜአ/ የብልጽግና ፓርቲ በአገር ጉዳይ የዳር ተመልካች የነበረውን የፖለቲካ ስርአት በመቀየር ሁሉንም አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ስርዓት ይዞ የመጣ ፓርቲ መሆኑን የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና የብልጽግና ጉባኤ ተሳታፊ ከድር ጁሃር ገለጹ፡፡

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ እና የብልጽግና ጉባኤ ተሳታፊ ከድር ጁሃር፤ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ የነበረው ኢህአዴግ አራት ብሔራዊ ድርጅቶችን ብቻ በማሳተፍ ሌሎችን "አጋር" በሚል በአገር ጉዳይ የዳር ተመልካች በማድረግ ለበርካታ ዓመታት መርቷል።

በወቅቱ አራቱ ግንባር (ህወሃት፣በአዴን፣ኦህዴድ እና ዴኢህዴን) ከመሰረቱት ኢህአዴግ በስተቀር ሌሎች አጋር የሚባሉት ድርጅቶች በሌሉበት የተወሰነውን እንዲፈፅሙና እንዲያስፈፅሙ ይገደዳሉ።   

በዚህም ምክንያት ብዙሃኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ኩርፊያ ውስጥ እንዲገባ በማድረጉ ፓርቲው ለመፍረሱ ምክንያት መሆኑን አቶ ከድር ይናገራሉ።

በወቅቱ የነበረው ዋልታ ረገጥነትም ለኢህአዴግ መፍረስና ለብልጽግና ፓርቲ በአዲስ አስተሳሰብ መወለድ ምክንያት መሆኑን ያብራራሉ።

የህዝብ ብሶት መብዛት፣ በሌሎች ክልሎች መካከል በመግባት ውሳኔ እስከ ማስቀየር የነበረው ሂደትም ሁሉንም አካታች ለሆነው ብልጽግና ፓርቲ መመስረት ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።

ብልጽግና በእስካሁኑ ሂደቱ በርካታ ግቦችን ማሳካቱን የገለጹት አቶ ከድር የመንግስት አደረጃጀትን እንደገና ለህዝብ አገልግሎት በሚመጥን መልኩ ማደራጀቱን አንስተዋል፡፡

በተለይም በፍትህ ተቋማት እና በመከላከያ ሰራዊት ላይ የተደረገው ሪፎርም ታላቅ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን አንስተዋል።    

በርካታ ውስብስብ ችግሮች የነበሩበትን የህዳሴ ግድብ እውን እንዲሆንና ሃይል እንዲሰጥ ማድረግም ብልጽግና ካከናወናቸው ስኬታማ ተግባራት መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በአገር ደረጃ እየተከናወኑ የሚገኙ ወሳኝ የልማት ስራዎችና የቱሪስት መስህቦችም ሌላኛው የስኬት ማሳያዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ከምስረታው ጀምሮ በርካታ ስኬቶችን ቢያስመዘግብም የተለያዩ ተግዳሮቶችንም በድል መወጣቱን አቶ ከድር ገልጸዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና የአንበጣ መንጋ ፓርቲው አገራዊ የልማት ዕቅዱን በሚፈልገው መጠን እንዳያሳካ እንከን ሆኖት ማለፉን ጠቅሰዋል።

የኑሮ ውድነት እና የብር የመግዛት አቅም ዝቅ ማለት ሌላኛው ፈተና መሆኑንም ገልጸዋል።

ሆኖም ብልፅግና በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ ድል ያደረገ የኢትዮጵያን ልማትና ልእልና ለማሳካት በጥሩ መሰረት ላይ የሚገኝ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በርካታ ድሎችን በማስመዝገብ የገጠሙትን ተግዳሮቶች በጥበብ እያለፈ መሆኑን ጠቅሰው አሁን ላይ የመጀመሪያ ጉባኤውን ለማካሄድ በሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማካሄድ መሪዎቿን ከሰየመች በኋላ እንዲሁም በአሸባሪው ህወሃት ተደቅኖባት ከነበረው የመፍረስ አደጋ ተሻግራ የሚደረግ በመሆኑ በተለየ አጋጣሚ የሚጠቀስ ጉባኤ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ መልኩም ከዚህ ቀደም አጋር ተብለው በኢትዮጵያ ጉዳይ የዳር ተመልካች የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች በነጻነት በመሳተፍ በፓርቲው መምረጥና መመረጥ በሚችሉበት ሂደት ውስጥ ሆኖ መካሄዱ ጉባኤውን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም የሚያካሂደው ጉባኤ በዋናነት በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ መሰረተ ልማቶችና የተፈናቀሉ ወገኖች በዘላቂነት የሚቋቋሙበት ጉዳይ ላይ ዋነኛ ትኩረቱን አድርጎ ሊወያይ እንደሚችል ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በአገር ደረጃ የሚታየውን የኑሮ ውድነት ችግር በመፍታት ረገድ ተወያይቶ አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

ብልጽግና ፓርቲ ከመጋቢት 2 እስከ 4 ቀን 2014 ዓ.ም "ከፈተና ወደ ልዕልና" በሚል መሪ ሃሳብ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ያካሂዳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም