ከብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ ዘላቂ ሰላም በማስፈን የዜጎችን መሰረታዊ ችግር የሚፈታ ውሳኔ ይጠበቃል - አስተያየት ሰጪዎች

82

ድሬደዋ/ መቱ / ሶዶ፤ የካቲት 30/2014 (ኢዜአ) ዘላቂ ሰላምን በማስፈን የዜጎችን መሠረታዊ የኑሮ ችግሮችን የሚያስችል ውሳኔ ከብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ እንደሚፈልጉ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።

የመቱና የወላይታ ሶዶ ከተሞች ነዋሪዎች ደግሞ ከጉባኤው ብልሹ አሰራርን አጥብቀው የሚታገሉና የኑሮ ውድነትን ለማርገብ የሚተጉ ጠንካራ አመራሮችን ለማምጣት የሚያስችሉ ውሳኔዎች ይጠብቃሉ።

 ከድሬዳዋ ነዋሪዎች መካከል መምህርት መርሻዬ ባዩ  ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ፓርቲው በህዝብ እውቅና አግኝቶ ሀገርን እየመራ መሆኑን ጠቁመው፤ በጉባኤው  ዜጎች በሰላም ወጥተውና ሰርተው መግባት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ተወያይቶ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።

''በየጊዜው የምንሰማው መፈናቀል፣መሰደድና መሞት መቆም አለበት ፤ፓርቲው ለዚህ መሠረታዊ ጉዳይ መፍትሄ መስጠት አለበት'' ብለዋል፡፡

አቶ አቡበከር አህመድ  በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ታስቦ  የተቋቋመው  የምክክር ኮሚሽን በዚህ ወቅት አስፈለጊ መሆኑን ጠቅሰው፤  ፓርቲው  በሚካሄደው  ጉባኤ ኮሚሽኑ በገለልተኝነትና በታዓማኒነት እንዲሰራ የሚያስችል ውሳኔ ማሳለፍ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

 ህዝብ በነቂስ ወጥቶ የመረጠው ፓርቲ የህዝብን መሠረታዊ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ ትርጉም ባለው መንገድ ለመፍታት የሚያግዙ ውሳኔዎች ማሳለፍ እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ ወይዘሮ ዘነቡ ፋንቱ የተባሉ ነዋሪ ናቸው።

ጉባኤው ህዝብን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ ለሚገኘው የኑሮ ውድነት አስቸኳይ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል ውሳኔ ይሰጣል የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል።

ጎዳና ላይ በጋሪ አልባሳት እየሸጠ ቤተሰቡን እንደሚያስተዳድር የተናገረው ወጣት ያሲን ዑመር በበኩሉ ፤የብልጽግና ፓርቲ  የሥራ አጥነት ችግሮች  ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት ወጣቱ በሀገር ዘላቂ ሰላም ፣ ልማትና የሀገር ህልውናን ማረጋገጥ ላይ የድርሻውን እንዲወጣ ውሳኔ ማሳለፍ እንዳለበት ጠቁሟል።፡

 ''የምንፈልገው ሰርተን ራሳችንንና ሀገራችንን መለወጥ ነው'' ያለው ወጣት ያሲን፤  ፓርቲው ለዚህ ዓላማችን መሳካት ከጎናችን መሆኑን በውሰኔው ማሳየት አለበት ብሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ   ከመቱ ከተማ  ነዋሪዎች  መካከል ወጣት ፍፁም ሰውነት በሰጠው አስተያየት ፓርቲው ውስጡን በማጥራት ሕዝቡንና ሀገርን ሲጎዳ የነበረውን የሌብነትን ከሕዝቡ ጋር ሆኖ በቁርጠኝነት መታገል የሚያስችል  ውሳኔ ከጉባኤው  እንደሚጠብቅ ለኢዜአ ተናግሯል።

መምህር ዮሐንስ ከበደ በበኩላቸው፤ ለሀገር አንድነት መጠናከር ወሳኝ የሆኑና ምቹ መደላደልን ሊፈጥሩ የሚችሉ አቅጣጫዎች ከፓርቲው ጉባኤ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ብልፅግና በጉባኤው ውስጡን ከብቃት፣ ከዕውቀት፣ ከአመለካከትና ሌሎች ወሳኝ እሴቶች አንፃር በደንብ መፈተሽ ይኖርበታል ብለዋል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ሕዝቡን በከፍተኛ ሁኔታ ያማረሩ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የአድልዎና ዝቅተኛ የአገልጋይነት መንፈስ   ሕዝቡን ባሰተፈ ሁኔታ ለማቃናት ፓርቲው በጉባኤው ቢያተኩርበት መልካም ነው ያሉት ደግሞ ወይዘሮ የኋላሸት ዓለሙ ናቸው።

በሌላ በኩል የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ አብርሃም ባቾሬ ፤ ፓርቲው በመስራች ጉባኤው የኑሮ ውድነት መንስኤ ላይ በመወያየት   ዘላቂ መፍትሄ ያመቻቻል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

ህገወጥ የግብይት ስርዓቱ መሻሻል እንደሚገባው ጠቁመው  ህገወጦችን በህግ የሚያስጠይቅ የተሻለ አሰራር እንዲዘረጋም ጠቁመዋል።

ብልፅግና ከባድ ፈተናዎችን በጠንካራ ትግል እያሸነፈ የመጣ ተስፋ የሚጣልበት ፓርቲ ቢሆንም ያነገበውን ተልዕኮ በአግባቡ እንዳይወጣ እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮች መኖራቸውን  ያነሱት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ብርሃኑ ጪሻ ናቸው።

ይኸውም በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች  የኑሮ ውድነትና የኢኮኖሚ አሻጥር ተጠቃሽ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጉባኤው  ችግሩን ነቅሶ በማውጣት ገበያን ማረገብ የሚያስችል ዘላቂ የመፍትሄ ሃሳብ ማምጣት በሚያስችሉ አጀንዳዎች ላይ ይወያያል ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋልል።

ወይዘሮ ዘይባ ከድር በበኩላቸው፤  ህዝቡ ኑሮ ጣራ ነክቶበት በልቶ ማደር በተቸገረበት ወቅት ፓርቲው ጉባኤ ማካሄዱ ያሉ ችግሮች ላይ በግልጽ ተወያይቶ ለመፍታትና ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም