ፓርቲው በጉባኤው ኢትዮጵያን ለማሻገር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ውሳኔዎችን ሊያሳልፍ ይገባል

70

አርባምንጭ የካቲት 30/2014 (ኢዜአ ) ብልፅግና ፓርቲ በሚያካሄደው መደበኛ ጉባኤ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ኢትዮጵያን ከተደቀኑባት ፈተናዎች ለማሻገር የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ውሳኔዎችን ሊያሳልፍ ይገባል ሲሉ የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች አመለከቱ ።

የብልፅግና ፓርቲ ከመጋቢት 2 ቀን 4014 ዓም ጀምሮ የሚያካሄደውን መደበኛ ጉባኤ አስመልክቶ ለኢዜአ ከአርባምንጭ ነዋሪዎች ጋር ቃለ ምልልስ አካሂዷል።

አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማው ነዋሪዎች  እንዳስታወቁት ፓርቲው በሚያካሂደው መደበኛ ጉባኤ ኢትዮጵያ ያሉባትን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት በዘላቂነት መፍትሔ ሊያስገኙ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አቅጣጫዎች ሊያስቀምጥ ይገባል ።

ከከተማው ነዋዎች መካከል አቶ ደረጀ ካሳሁን  እንዳሉት ጉባኤው የፓርቲው አመራሮች ወሳኝ የሆኑ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የተሻለ ተግባቦት የሚፈጥሩበት እንዲሁም አሻጋሪ ሀሳብ ያላቸውና ብቁ አመራሮች ነጥረው የሚወጡበት ሊሆን ይገባል ፡፡

ፓርቲው በመደበኛ ጉባኤ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶችን በመፍታት ኢትዮጵያን  ከተደቀኑባት ፈተናዎች ለማሻገር  የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ  ያተኮሩ ውሳኔዎችን ሊያሳልፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።

"ብልፅግና በህዝብ ድምፅ የተመረጠና ሀገርን እየመራ ያለ ፓርቲ እንደመሆኑ በተለይ በየአካባቢው የሚቀሰቀሱ ግጭቶች ቆመው ዜጎች በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢዎች የመዘዋወርና የመስራት መብታቸው ተከብሮ የሚኖሩበትን መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል ውሳኔ በጉባኤው ሊያሳልፍ  ይገባል" ብለዋል ።

በጉባኤው ኢትዮጵያ ሠላሟ የተረጋገጠና አብሮነት የሰፈነባት ሀገር ሆና የምትቀጥልበትን መደላድል ለመፍጠር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ውሳኔ ሊያሳልፍ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።

ፓርቲው የውስጠ ዴሞክራሲያዊ አንድነቱን በማጠናከር እንደ ሀገር ማዕከላዊነቱን የጠበቀ ወጥ የሆነ አቋምና አጀንዳ ኖሮት እንዲመራ በትኩረት መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል ፡፡

አቶ ደረጀ  እንዳሉት ብልፅግና ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶቹ ላይ ተወያይቶ መፍታት ከቻለ ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት የፈተና ወቅት ማሻገር የሚችል ፓርቲ ነው ፡፡

የፓርቲው አደረጃጀትና ያለው ህዝባዊ መሰረት ደሞ ለዚህ ምቹ ሁኔታዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል ፡፡

"ችግሮች ሲፈቱ ለጊዜያዊ ማስታገሻነት ሳይሆን በማያዳግምና ዘለቄታ ባለው አግባብ መሆን አለበት" ያሉት አቶ ደረጀ ወሳኝ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ከህዝቡ ጋር ተናቦ መስራት እንደሚያስፈልግ ነው የጠቆሙት ፡፡

አቶ አለማየሁ መንግስቱ በበኩላቸው ፓርቲው በሚያካሂደው ጉባኤ እየከፋ የመጣውን የኑሮ ውድነት ፣ ሥራ አጥነትና ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ተወያይቶ መፍትሔ ለማበጀት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ሊያሳልፍ እንደሚገባ አመልክተዋል ፡፡

"ፓርቲው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በርካታ ችግሮችን እያለፈ እዚህ ደርሷል" ያሉት አቶ አለማየሁ አሁንም ወሳኝ የሆኑ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት በመስጠት ሀገራዊ ሠላም ፣ አንድነትና ልማትን ማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ሊያሳልፍ እንደሚገባ አመልክተዋል ።

አክለውም "መንግስት ችግሮቻችንን ከመሠረቱ ለመቅረፍ የሚያደርገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን ሁሌም ከጎኑ እንቆማለን" ብለዋል ፡፡

ወጣት ዐባይነህ ሞርካ በበኩሉ "ጉባኤው ኢትዮጵያ በጦርነት ምክንያት የገጠሟትን ችግሮችም ሆነ የውጭ ጫናዎች ተቋቁማ ማለፍ የምትችልበትን የመፍትሔ አቅጣጫ ያስቀምጣል ብዬ አምናለሁ" ብሏል ፡፡

"ፓርቲው ኢትዮጵያ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠላቶቿ የተደቀነባትን ፈተና ማለፍ በሚቻላት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ  እጠብቃለሁ " ሲል  ወጣት ዐባይነህ  አመልክቷል ።

"ፓርቲው ሀገሪቱን እየመራ ያለ እንደመሆኑ የህዝቡን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ የሁላችንም ተሳትፎ ያስፈልጋልም" ሲል አክሏል ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም