ዩ ኤስ ኤይድ በጦርነት ለተፈናቀሉ ኢትዮጵያዊያን የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

71

 የካቲት 30/2014 (ኢዜአ)  የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት /ዩ ኤስ ኤይድ/ በአፋርና አማራ ክልሎች በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች የ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ትሬሲ አን ጃኮብሰን፤ ድጋፉን ለአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስረክበዋል።

የተደረገው ድጋፍ ከ10 ሺህ በላይ ተፈናቃይን ተጠቃሚ የሚያደርግ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያለው 250 ሜትሪክ ቶን የምግብ እና ሌሎች ቁሳቁሶች መሆኑን አምባሳደሯ ገልጸዋል።

የአሜሪካ መንግስት ላለፉት ዓመታት ከ900 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጓንም አስታውሰዋል።

የአሜሪካ መንግስት በችግር ውስጥ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነሲቡ ያሲን፤ በጦርነቱ ምክንያት የተጎጂዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑን ጠቅሰው መልሶ ለማቋቋምና ለማገዝ የሁሉም ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

ከመንግስት ባለፈ የህዝብና የአጋር ድርጅቶች የተጠናከረ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው የአሜሪካ መንግስት ላደረገው ድጋፍም አመስግነዋል።

የተደረገው ድጋፍም በሁለቱ ክልሎች ተፈናቅለው በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ተደራሽ ይሆናል ብለዋል።

በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎች አሃዝ እና ድጋፉ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ልዩ ትኩረት ለሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች በቅድሚያ ተደራሽ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም