በጋምቤላ በምርት ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 64 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

89

ጋምቤላ የካቲት 30/2014(ኢዜአ) በመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎችና በሲሚንቶ ምርት ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 64 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የጋምቤላ ክልል ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የዋጋ ንረት  የሚፈጥሩ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስቧል ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኦኬሎ ኡቦንግ ለኢዜአ እንደገለጹት አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች በጋምቤላና አካባቢው ሰሞኑን በኢንደስትሪ ምርቶች ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ሕዝቡን በማማረር ላይ ናቸው።

በተለይም በዘይት፣ በስኳር ፣ በዳቦ ዱቄትና ሌሎችም ምርቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መደረጉን ገልጸዋል።

በግንባታ ፍጆታ ዕቃዎችም ላይ በተመሳሳይ መልኩ የዋጋ ጭማሪ መደረጉንና በተለይም ከአንድ ሳምንት በፊት የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ 750 ብር የነበረው አሁን ላይ ወደ ከአንድ ሺህ ብር በላይ መድረሱን አስታውቀዋል።

ቢሮው ችግሩን ግምት ውስጥ በማስገባት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ ክትትል በማድረግ በ64 የንግድ ድርጅቶች ላይ የንግድ ፍቃድን ከመሰረዝ ጀምሮ የማሸግና ሌሎች አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዱን ተናግረዋል።

ቢሮው በቀጣይም ከድርጊታቸው በማይቆጠቡ ነጋዴዎች ላይ ክትትል በማድረግ  ተመሳሳይ  እርምጃ እንደሚወሰድ ምክትል ኃላፊው አስጠንቅቀዋል።

ከጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ባኑን ታታ በሰጠው አስተያየት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በዘይት፣ በዳቦ ዱቄት፣ በስኳር፣ በሰሚንቶና በሌሎች ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ገልጿል።

"የዋጋ ንረትን ለማርገብ መንግስት ከህዝቡ ጋር በመተባበር መሰራት አለበት" ብለዋል።  

በተለይም አሁን ላይ የምግብ ዘይት ዋጋ መጨመሩ ብቻ ሳይሆን  የምርት እጥረት ጭምር መኖሩን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ጽሃይ ውለታው ናቸው።

መንግሥት የምግብ ዘይትን ጨምሮ በሌሎች ፍጆታ ምርቶችን ዋጋ ለማረጋጋት እንዲሰራ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም