አድሱኝ- ወርቅና አልማዝ ነኝ…

424

በወንድማገኝ ሲሳይ (ሀዋሳ ኢዜአ)


በመንግሥት የተነደፈው የ10 ዓመቱ መሪ ዕቅድ በአጠቃላይ ሀገራዊ ኢኮኖሚው ለማሳደግ መዘጋጀቱ ይታወቃል፤ በዕቅዱ የግብርናውን ዘርፍ በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ ነው፤ ይህን እውን ለማድረግም በየደረጃው እንቅስቃሴው ቀጥሏል።ሀገራችን በነደፈችው ዕቅድ በተለይ  የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ትኩረት ከተሰጣቸው አንዱ ቡና ነው።

 ከቡና የሚጠበቀውን ገቢ ለማግኘት ከችግኝ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ጥራት አጠባበቅ ሂደት የሚሳተፉ አካላት   ድርሻቸውን መወጣት  ይጠበቅባቸዋል።

ሀገሪቱ ከቡና ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ ካደረጉት ዋና ዋና ተግዳሮቶች መካከል በቡና ተክል ከተሸፈነው መሬት አብዛኛው በእርጅና ምክንያት አነስተኛ ምርት መስጠቱ  ተጠቃሽ ነው።

ኢትዮጵያ ቡናን ለዓለም አምራች ሀገራት  ያበረከተች ብትሆንም ከምርቱ ማግኘት ያለባትን ያህል ሳትጠቀም  ቆይታለች፤ ምንም እንኳን በቅርቡ ገቢዋን እያደገ ቢመጣም።

የቡና ልማት በስፋት ከሚካሄድባቸው የሀገሪቱ ክፍሎች መካከል የደቡብ ክልል አንዱ ነው።

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንደሚሉት፤ በክልሉም ሆነ እንደ ሀገር ያረጀ ቡና በስፋት መገኘቱ የዘርፉን ምርትና ምርታማነት ይቀንሳል።

ይህንን ታሳቢ በማድረግ  ዘንድሮ በክልሉ ቡና አምራች ዞኖችና  ልዩ ወረዳዎች ሰፊ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የቡና ተክልን በመጎንደልና ነቅሎ በመትከል የማደስ ሥራ በስፋት እየተካሄደ ይገኛል ይላሉ።

ይህም እንቅስቃሴ የቡና ልማቱን በየደረጃው በማስፋፋትና በማጠናከር የአምራቹን፣የንግዱን ማህበረሰብና የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ በክልሉ 337 ሺህ 358 ሄክታር በቡና የተሸፈነ ሲሆን፣ ከዚህ ውሰጥ  239 ሺህ 529 ሄክታር የሚሆነው ምርት በመስጠት ላይ ይገኛል፤ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚበልጡ አርሶ አደሮችም የቡና ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ ናቸው፤ በየዓመቱም ከ1ነጥብ 6ሚሊዮን ኩንታል  በላይ ቡና  ይመረታል።

ምርቱ ክልሉ ካለው አቅም አንፃር ዝቅተኛ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ኡስማን፣  በቡና ተክል ከተሸፈነው መሬት ውስጥ  እስከ 40 በመቶ የሚሆነው ያረጀ ቡና መሆኑን፣ ቡና ከእርጅና ባሻገር በበሽታና በእንክብካቤ ጉድለት በመጎዳታቸው የሚፈለገውን ያህል ምርት ማስገኘት አለመቻሉ በምክንያትነት ጠቅሰዋል።

በዚህም ምክንያት አርሶ አደሩ ቡናን በስፋት አምርቶ ለገበያ ማቅረብ ካለመቻሉም በላይ ሀገሪቱ ከዘርፉ በምታገኘውየውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ ነው የተናገሩት።

ችግሩን ለመፍታት  እንዲያገዝ ክልላዊ  የቡና ጉንደላ ንቅናቄ ሰሞኑን በከምባታ ጠምባሮና  ወላይታ ዞኖች በይፋ ተጀምሯል። 

በዚህም በክልሉ የቡናን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ያረጀ ቡናዎችን በሁለት መንገዶች ለማደስ እየተሰራ ይገኛል፤  አንደኛው ያረጀውን ቡና መጎንደል ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ነቅሎ ተከላ ነው።

ንቅናቄው በክልሉ በሚገኙ 11 ዞኖችና ስድስት ልዩ ወረዳዎች እየተካሄደ ሲሆን፤ ሥራውን በሁሉም አካባቢዎች እንደሚስፋፋ የተናገሩት ኃላፊው፣ አርሶ አደሩ በሥራዎቹ  በማሳተፍ  የቡና ችግኞች ተከላ ጭምር ይካሄዳል ብለዋል።

አሁን ላይ  ወደ 90 ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ችግኞች እየተዘጋጁ መሆናቸውንና ከዚህ ውስጥ 40 ሚሊዮን  ችግኞች በአዲስ ተከላ ፣ቀሪው ደግሞ በነቅሎ ተከላ የሚከናወኑ ናቸው።

የክልሉ  ቡናና ቅመማ ቅመም ባለሥልጣን   ዋና ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን ከድር በበኩላቸው ''ያረጀ ቡና መታደስ አለበት፤ ቡና በተፈጥሮ አድሱኝ ነው የሚለው፤ ካደሳችሁኝ አገለግላችኋለሁ ፣እጠቅማችኋለሁ። ካደሳችሁኝ ወርቅና አልማዝ ነኝ ይላል" ሲሉ አስረድተዋል።

''ንግግሩን ከቡና ጋር በቅርበት የሚኖር ሰው ያዳምጠዋል፣ይሰማዋል፣ይረዳዋል የሚያስተላልፈው ድምፅ አልባ መልዕክት ነውና'' ሲሉም አክለዋል።

ቡና ሲጎነደል የራሱ አሰራር አለው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤  ያረጀ ቡና ሲጎነደል በርከት ያሉ ቅጥያዎችን ያወጣል፤  ሌላው ተክል ሲጎነደል ለምን ተነካሁ ብሎ እዛው ይሞታል ፣ቡና ግን በአንፃሩ ይለመልማል  ሲሉ ነው ያብራሩት።

ያረጀ ቡና ዛፍ  ሲጎነደል ከሚያወጣቸው በርካታ ቅጥያዎች እንደ ሁኔታው ሁለትና ሶስት ቅጥያዎች ብቻ እንዲቀሩት ይደረጋል፤ ይህ ሲያድግ አዲስ ከተተከለ ቡና ችግኝ በምርታማነቱ የተሻለ እንደሚሆን ነው ያመለከቱት።

ከዚህ በመነሳት  ዘንድሮ የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ  10 ሺህ 675 ሄክታር ላይ ያረጀ ቡና ጉንደላ በማካሄድ ለማደስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁን በተካሄደው እንቅስቃሴ ከ3 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ የቡና ማሳ ላይ መጎንደሉን አስረድተዋል።

ይህም ተግባር  በቡና ልማት የተሻለ ልምድ ያላቸውን አርሶ አደሮች ማሳ ያማከለ መሆኑን ጠቅሰው፣ስራው የቡና ጥራት በማሳደግ በቡና ልማት የተሰማሩ በርካታ አርሶ አደሮች ህይወት ከመቀየር ባለፈ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚደግፍ አመልክተዋል ።

በወላይታ ዞን ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ወርሙማ ቀበሌ ነዋሪ ማሴቦ ማዴቦ በሰጡት አስተያየት ፤በቡና ልማት መሳተፍ ከጀመሩ ሰባት ዓመታትን ማስቆጠራቸውን ጠቅሰው፤  በነዚህ  ዓመታት  ቡና በስፋት በማልማት ተጠቃሚ እንደሆኑ ነው የሚናገሩት።

አርሶ አደሩ እንዳሉት፤ ዘንድሮ  የቡና ምርታማነታቸውን ለማሻሻል በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ የሚገኘውን 200 እግር ቡና ጎንድለዋል፤ ለልማቱ አመቺነትም ለቡና ጥላ የሚሆን የሙዝ ችግኝ በመትከልና የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀም  እየተንከባከቡ ይገኛሉ።

''የግብርና ባለሙያዎች ባሳዩን መሠረት ቡናው ተገቢ ምርት እንዲሰጠኝ የተለያዩ ተግባራት በማከናወን ላይ ነኝ፤ሌሎችም ከእኔ ልምድ ወስደው በዚህ ስራ ገብተው ያረጀ ቡናዎችን እንዲጎነድሉ ለማስተማር ጭምር እየሰራሁ ነው ያለሁት'' ብለዋል።

አርሶ አደሩ ከቡና ልማት ሥራ በተጓዳኝ የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎችን በመትከል ውጤታማ መሆናቸውን  ጠቁመዋል።

ከአራት አስርት ዓመታት በላይ ቡናን ሲያለሙ መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ በከምባታ ጠምባሮ ዞን የቃጫ ቢራ ወረዳ ምስራቅ ሌሾ ቀበሌ ቡና አምራች አርሶ አደር ሃይሌ አርጊቾ ናቸው።

ከቡና ባገኙት ገቢ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ከመገንባት ባለፈ ስምንት ልጆቻቸውን እስከ ከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ድረስ በማስተማር ለወግ ማዕረግ ማብቃታቸውን ነው ያመለከቱት።

በአሁኑ ወቅትም የቡና ልማቱን በ3 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት እያካሄዱ ቢሆንም አብኛዛው የቡና ዛፋቸው በማርጀቱ ምርታማነታቸው እየቀነሰ መምጣቱን ጠቁመው፤ በመጎንደል በአዲስ ለመተካትና አዳዲስ ቡና ለመትከል በመሥራት ላይ  እንደሚገኝ ተናግረዋል።

 ''ዘንድሮ ብቻ 1 ሺህ 261 አዲስ የቡና ችግኞች ለመትከል ዝግጅት አድርጊያለሁ፣ ለዚህ ተከላ የሚሆን ቁፋሮም ጨርሼያለሁ።'' ያሉት አርሶ አደሩ፤ በግብርና ባለሙያዎች እገዛ 360 እግር ቡና መጎንደላቸውንና ቀሪውንም 200 እግር ለመጎንደል መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል። 

እንደ አርሶ አደሩ ገለጻ፤  በዓመት 66 ኩንታል እሸት ቡናና 32 ኩንታል ደረቅ ቡና በመሰብሰብ ለገበያ ያቀርባሉ። 

ሌላኛው የቀበሌው አርሶ አደር ተስፋዬ ዱላ ፤ለረጅም ዘመናት በቡና ልማት ሲሳተፉ መቆየታቸውን ገልጸው፤ አሁን ላይ በሁለት ሄክታር ይዞታቸው ለይ የሚገኘውን የቡና ምርት ለማሳደግ 300 እግር ቡና በመጎንደል እየተንከባከቡ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት።

አርሶ አደሩ እንዳሉት፤ ከአሁን በፊት ያካሄዱት የቡና ጉንደላ ምርታማነታቸውን እጥፍ እንዳሳደገላቸውና በዓመት ከምርቱ ሽያጭም  ከ30 ሺህ ብር በላይ ትርፍ  ያገኛሉ።

በዞኑ 74 ሺህ አርሶ አደሮች በቡና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብር እየተሳተፉ እንደሚገኙ የገለጹት ደግሞ የከምባታ ጠምባሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መለሰ ሀጪሶ ናቸው።

ባለፉት ዓመታት የዞኑ አርሶ አደሮች የቡና ምርታማነታቸው በመቀነሱ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ ሳይሆኑ መቅረታቸውን አስታውሰዋል።

ችግሩን ለመፍታት የቡና ነቀላ፣ ጉንደላና እድሳት ውስጥ በስፋት ገብተናል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤በተለይ አርሶ አደሮች በባለሙያ ታግዘው ልማቱን  ለማስፋፋት መሥራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የስፔሻሊቲ ቡና ልማትን በተመረጡ ቃጫ ቢራ፣ሀደሮ ጡንጦ፣ቀዲዳ ጋሜላ፣ጠምባሮና ዳምቦያ ወረዳዎች ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።

''አድሱኝ- ወርቅና አልማዝ ነኝ''  የሀገር ኢኮኖሚ ዋልታ ቡና!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም