አንድ ሺህ ብር..…‼

452

አንድ ሺህ ብር..…‼

በያንተስራ ወጋየሁ (ዲላ ኢዜአ)

ቦታው ዲላ ከተማ ትልቁ ግንብ ገበያ ነው። ገበያው ዛሬም ትርምሱና ሁካታው አልተቀየረም። የዲላ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ምንትዋብ ተሰማ ሁሌም እንደሚያደርጉት የአቅማቸውን ለመሸመት የገበያ ቦታው ላይ ቢገኙም የዛሬው የገበያ ሁኔታ ረብሿቸዋል።

ወይዘሮ ምንትዋብ አታክልቱ በአይነት በአይነቱ ወደ ተደረደረበት ስፍራ ፊታቸውን ያዞሩና ለመጠጋት አስበው ሲሳቀቁና  ሲረበሹ ተለዋዋጭ ስሜታቸውንና ድንጋጤያቸው ከፊታቸው ላይ ይነበባል። ለሚያያቸው የአዕምሮ እክል ያለባቸው አልያም አንዳች ነገር የነካቸው እንጂ በዋጋ ውድነት አንድ ሺህ ብር ይዘው ገበያ በመውጣት የሚሸምቱት ግራ የገባቸው እና በትካዜ የተረበሹ እናት አይመስሉም።  

ወይዘሮዋ  ከቀናት በፊት  አንድ ሺህ ብር ገበያ ይዘው ወጥተው 5 ሊትር ዘይት በተቀረው ድግሞ ጎመኑን ፣ቃሪያውን ፣ቅመማ ቅመሙን ሽሮና በርበሬያቸውን ገዝተው መሰንበቻቸውን ቢያሳልፉም ዛሬ ላይ ግን የዘይቱ ዋጋ ብቻ አንድ ሺህ ብር  በመሆኑ ትካዜ ውስጥ ከቷቸዋል።

እሳቸውን ጨምሮ ሶስት ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩት ወይዘሮ ምንትዋብ 1ሺህ 300 የባለቤታቸው ጡረታ ተጨማሪ አንድ ሺህ ብር የልጃቸው ድጎማ በድምሩ 2ሺህ ሺህ 300 ብር ወርሃዊ ገቢ አላቸው። 2 ሺህ 300 ብር ወርሃዊ ወጭያቸውን መሸፈን አቅቶት እድር፣ እቁባቸውን ካቆሙ ሰንብተዋል። አመት በዓል ጠብቀው የሚቀይሩትን ልብስም  ቢሆን ገዝተው መጠቀም ካቆሙ  ዓመታት አልፈዋል።

የኢዜአ ሪፖርተር ገበያውን ለመቃኝት በወጣበት ሰዓት የወይዘሮ ምንትዋብን ስሜት መታዘብ ቻለ እንጅ   ስሜቱን  በርካታ የኢትዮጵያ እናቶች የሚጋሩት ነው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ አለምን ባደረሰው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ፣ ጦርነት፣ ድርቅና  የምርት መቀነስን ተከትሎ  ምክንያታዊ የሆነ የዋጋ ጭማሪ እንደሚከሰት የሚጠበቅ ቢሆንም ከምክንያቶች ያለፈና ሰሚ ያጣው የዋጋ ጭማሪ በተለይ በታችኛውና በመካከለኛው የገቢ ደረጃ ያለውን የህብረተሰብ ክፍል በእጅጉ እየተፈታተነ ነው።

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመማሪው ዶክተር ታምራት ታደሰ አሁን የሚስተዋለው የዋጋ ንረት ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪን በመቆጣጠር ብቻ የሚፈታ አይደለም ይላሉ።

በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት በሽታ ድርቅና ጦርነት የማይናቅ የሰው ኃይልና የሚለማ መሬት ከምርት ውጭ መሆኑ ሳያንስ የብር የመግዛት አቅም ማሽቆልቆልና የውጭ ምንዛሬ ክምችት አናሳ መሆን ከአለም አቀፍ ተጽዕኖና ማዕቀብ ጋር ተዳምሮ ለምርት መቀነስና ለውስብስብ የገበያ ስርዓት መዳረጉን ያስረዳሉ።

 ህገ ወጦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ለአንድ የችግር ዘለላ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ በድምር ውጤቱ ላይ ትርጉም ያለው መፍትሄ ይዞ አይመጣም ሲሉ ይሞግታሉ። የዋጋ ንረቱን በዘላቂነት ለመፍታት መንግስትና ህዝብ በሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች የሞት ሽረት ትግል ማድረግ እንዳለባቸው በመጠቆም። "

ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የምግብ ዋስትናውን ሊያረጋግጥ በሚችል የግብርና ስራ መሳተፍ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው የሚሉት ምሁሩ፤ ''የአመጋገብ ስርዓንታችን በማስተካከል በስርዓተ ምግብ ውስጥ ያልተካተቱ ምግቦችን በማካተት ወቅቱን በብልሃት መሻገር ጠቃሚ ነው'' ብለዋል።

ቻይና ከዛሬ ግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት  ስር የሰደደው ድህነቷንና የምግብ እጥረትን ተቋቁማ ማለፍ የቻለችው ጠንካራ የስራ ባህል በመገንባትና የምግብ ስርዓቷን መቀየር በመቻሏ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ታምራት፤ይሁንና ሁለቱም አማራጮች ጊዜ የሚጠይቁ በመሆናቸው አሁን ለተፈጠረው አንገብጋቢ የዋጋ ንረትና የምርት እጥረት ጊዜያዊ መፍትሄ ለማበጀት መንግስት ምርት በድጎማ በማቅረብም ሆነ ገበያውን በማረጋጋት ጣልቃ መግባት ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት  ሰፋፊ እርሻዎችን ከመጠቀም ባለፈ  አሁን የተጀመሩ የውሃ አማራጮችን አሟጦ ለመጠቀም ጥረት ማድረግ ከመንግስት የሚጠበቅ መሆኑን አመልክተዋል።

"ነፍጥ አንስቶም ሆነ ስንቅ በማቀበል ወራሪውን ሃይል  መክቶ ያሳፈረ ህዝብ  ዛሬ ደግሞ ሞፈር ይዞ በድህነት መዝመትና ድል ማድረግ  አማራጭ የሌለው ጉዳይ" ነው ብለዋል።

ከዚህ ውጭ አንድ ወገን ብቻ መፍትሄ በመጠበቅ አልያም በመንግስት ላይ በማማረርና በማጉረምረም ሌላ አማራጭ መፈለግ ውጤቱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ከመሆን ውጭ እድል የለውም ሲሉ ሃሳባቸውን ይቋጫሉ።

 ከወዲሁ ለኑሮ ውድነቱ  መፍትሄ እናበጅለት፤ መልካሙ ቀን እስኪመጣ ትጋታችን ለችግሮቻችን ምላሽ ያመጣሉና ለአፍታም አንዘናጋ መልክታችን ነው ።ቸር ወሬ ያሰማን!!

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም