የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማጎልበት ለአገር ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ መስራት ይገባል

114

የካቲት 29/2014/ኢዜአ/ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማጎልበት ለአገር ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ሊሰራ እንደሚገባ በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ ገለጹ፡፡


ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን" እኔ የአህቴ ጠባቂ ነኝ" በሚል መሪ ሃሳብ በመላው ዓለም ለ111ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ46ኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡

የኢትዮጵያ ሴቶች ማህበር ቅንጅት ከፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር በመተባበር ቀኑን “የሴቶች ተሳትፎ በሰላምና ፀጥታ እንዲሁም የሲቪክ ማህበራት የሴቶችን መብቶች ለማስከበር ያላቸው ሚና” በሚል ርዕስ በፓናል ውይይት አክብሯል፡፡

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ሬሚ ማሬሾ በዚሁ ወቅት የፈረንሳይ መንግስት በስርዓተ ጾታ ላይ ያተኮሩ 19 ፕሮጀክቶችን በኢትዮጵያ በሚገኙ ዘጠኝ ክልሎች እየተገበረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ኤምባሲው በኢትዮጵያ የስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡“ዛሬ በስርዓተ ጾታ ላይ የሚሰራው ስራ ነገ ለአገር ዕድገት መሰረት ይሆናል" ሲሉም ነው አምባሳደሩ የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያ በፈጠራ፣ በሳይንስ፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካ ዘርፍ ላይ የሴቶችን ተሳትፎ በማሳደግ በአገር ግንባታ ሂደት የላቀ ሚና እንዲጫወቱ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

በተለይም በፖለቲካው መስክ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ከተቻለ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር እንደሚቻልም አስረድተዋል፡፡በዚህ ረገድ የፈረንሳይ መንግስት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ ወይንእሸት ገለሶ በበኩላቸው የሴቶችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማስከበር የሚከናወኑ ተግባራት በመንግስት ጥረት ብቻ ውጤታማ ሊሆኑ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ አኳያ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ ማህበራትና ግለሰቦች  በስርዓተ ጾታ እኩልነት ላይ ተሳትፎ  ማድረግ እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም