ታዳጊ ወጣቶችን በመጠቀም ለሽብር ተግባር ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ተያዙ

326

የካቲት 29 ቀን 2014 (ኢዜአ) ታዳጊ ወጣቶችን በመጠቀም የሽብር ተግባር ለመፈጸም በእንቅስቃሴ ላይ የነበሩ ሁለት የሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጭሮ ከተማ ፀጥታ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የጭሮ ከተማ ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሾይኢቢ ሀምዛ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የካቲት 27 ቀን 2014 ዓም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ላይ ነው።

ግለሰቦቹ “በጥሩ ክፍያ ስራ እናስቀጥራችኋለን” በሚል ከምዕራብ አርሲ ዞን ጎሎልቻ ወረዳ ጃራ ከተማ ሰባት ታዳጊ ወጣቶችን በማታ ወደ ጭሮ ከተማ ያመጧቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ታዳጊ ወጣቶቹን ወደ ከተማው ካመጧቸው በኋላ ወደ ጭሮ ወንዝ አካባቢ በመውሰድ ተልእኮ እየሰጧቸው ባሉበት ወቅት ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሰረት በጸጥታ አካላት ትብብር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

ግለሰቦቹ ከእይታ ለመሰወር ሲሉ ወደ ወንዝ አካባቢ ይዘዋቸው በመግባት በህብረተሰቡ ውሰጥ ስለሚፈጽሟቸው ተግባራት ያስረዷቸው እንደነበር ህጻናቱ መናገራቸውን ኃላፊው ተናግረዋል።

የታዳጊ ወጣቶቹ ቤተሰቦችም ከጃራ ከተማ ልጆቻችን በአንድ ቀን ጠፍተውብናል ሲሉ ማመልከታቸውን ከከተማው ፖሊስ ማስረጃ መቅረቡን ጠቁመዋል።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ውለው በጭሮ ከተማ ፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል ከአምስት ቀን በፊት ከሚኤሶ ከተማ ወደ ኦዳ ቡልቱም ወረዳ በለሊት ሰርገው ለመግባት የሞከሩ 10 የሸኔ ታጣቂዎች በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሀላፊው ተናግረዋል።

በሀገር ሰላምና ፀጥታ ማስከበር ሂደት ውስጥ የህብረተሰቡ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።