ፍርድ ቤቱ በባለስልጣናቱ ግድያ ጥፋተኛ በተባሉ ተከሳሾች ላይ ከ15 ዓመት እስክ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወሰነ

50

የካቲት 29/2014 (ኢዜአ) የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰኔ 15/2011 ዓ.ም በአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ግድያ ጥፋተኛ በተባሉ 31 ተከሳሾች ላይ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወሰነ።

በእነ ሻምበል መማር ጌትነት የክስ መዝገብ ተጠርጥረው ክስ ተመስርቶባቸው የፍርድ ሂደታቸውን ሲከታተሉ ከቆዩ 55 ተከሳሾች መካከል ቀደም ሲል 20ቹ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ተደርጓል።

እንዲከላከሉ ከተባሉት መካከል ደግሞ 4ቱ በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱ በቅርቡ መወሰኑ ይታወሳል።በቀረበባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃ ጥፋተኛ የተባሉት ቀሪ 31 ተከሳሾች ላይ ደግሞ ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በሚደርስ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም መሰረት 1ኛ ተከሳሽ ሻምበል መማር ጌትነት፣ 15ኛ ተከሳሽ በላይሰው ሰፊነው እና 44ኛ ተከሳሽ ልቅናው ይሁኔ በሌሉበት እያንዳንዳቸው በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ወስኖባቸዋል።

እንዲሁም ሙሉጌታ ፀጋዬ፣ ሃምሳ አለቃ አሊ ሀሰን እና ፈቃዱ ምትኩ የተባሉ 3 ተከሳሾች እያንዳንዳቸው በ18 ዓመት፤ ሻለቃ አዱኛ ወርቁ እና ሻምበል ታደሰ እሸቴ የተባሉ ተከሳሾች ደግሞ በ17 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

ፍርድ ቤቱ ሻምበል ውለታው አባተና ሃምሳ አለቃ አበበ መልኬ እያንዳንዳቸው በ16 ዓመት፣ እንዲሁም ሃምሳ አለቃ ሲሳይ ገላናው እና ሃምሳ አለቃ በላቸው ዘውዴ በ15 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አሳልፏል።ከዚህ ተጨማሪ ሃምሳ አለቃ አሰፋ ጌታቸውን ጨምሮ ሌሎች 18 ተከሳሾች ላይ እያንዳንዳቸው በ16 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት 23ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ባስቻለው ችሎት ወስኖባቸዋል።

ፍርድ ቤቱ ለተከሳሾቹ የማህበራዊ አገልግሎትን፣ የቤተሰብ ኃላፊነትን፣ ለሀገር የተከፈለ ዋጋን፣ የጤና ሁኔታ እንዲሁም በአብዛኞቹ ተከሳሾች ላይ የወንጀል ሪከርድን ከዚህ ቀደም አለመኖርን በቅጣት ማቅለያነት መያዙንም አመልክቷል።

በማክበጃነት ደግሞ በህብረትና በማደም ህገ-መንግስትና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል በመናድ ከህግ ውጭ ስልጣን ለመያዝ የተደረገን ሙከራ ማድረግ ከጥፋቶቹ መካከል ተጠቀሰው ይገኝበታል።

በሌሉበት በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ የተላለፈባቸው 1ኛ፣ 15ኛና 44ኛ ተከሳሾችን ፖሊስ ካሉበት አፈላልጎ በመያዝ ለማረሚያ ቤቱ እንዲያስረክብ ትዕዛዝ በመስጠት ፍርድ ቤቱ የዕለቱን ችሎት አጠናቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም