በነጭ ሣር ብሔራዊ ፖርክ ተከስቶ የነበረውን የእሳት ቃጠሎ መቆጣጠር ተቻለ

64

አርባ ምንጭ፤ የካቲት 28/2014 (ኢዜአ) በነጭ ሣር ብሔራዊ ፖርክ ተከስቶ የነበረው የእሳት ቃጠሎ ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር መቻሉን የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሽመልስ ዘነበ አስታወቁ።
ሥራ አስኪያጅ  ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ትናንት ከረፋዱ ጀምሮ በፓርኩ አካባቢ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ለመቆጣጠር የጋሞ ዞን ፣ የአርባ ምንጭ ከተማና ዙሪያ ወረዳ የጸጥታ አካላትና የፓርኩ ስካውቶች ከፍተኛ ርብርብ አድርገዋል።

በዚህም የእሳት ቃጠሎውን  ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር ቢቻልም 25 ሄክታር የሚሆነው የፓርኩ ተራራማ ክፍል መውደሙን አስታውቀዋል።

የእሳት አደጋውን ከዚህ በላይ ጉዳት እንዳያደረስ 300 የሚጠጋ የሰው ኃይል ብርቱ ርብርብ ማድረጋቸውን ገልጸው ለዚህም በፓርኩ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የእሳት ቃጠሎው መነሻ ከሰል ከሚያከስሉ እና የእንስሳት ሳር ፍለጋ ከገቡ ሰዎች ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ግምት እንዳለ ጠቁመዋል።

ይህንን ሕገወጥ ተግባር ለመከላከል  ከ"ፓትሮል"  ጥበቃ ባሻገር ፓርኩ ከአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ ከአስተዳደር አካላት ጋር በየወቅቱ ውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እንደሚያካሂድ አመልክተዋል

በቀጣይም ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ፣ ባለሀብቶች እና  ባለድርሻ አካላት በባለቤትነት መንፈስ ችግሩን ለማስቆም እንዲሰሩ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም