በመንገድ ሥራ ድማሚት ፍንዳታ የሰዎች ህይወት አለፈ

91

መተማ ፤ የካቲት 28/2014 (ኢዜአ) በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ ለመንገድ ሥራ አገልግሎት ተብሎ የተቀመጠ ድማሚት ፈንድቶ የሰዎች ህይወት ማሳለፉን   ፖሊስ አስታወቀ።

የወረዳው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ሃይሌ ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ጉዳቱ የደረሰው ትናንት ቀን 11 ሰዓት ተኩል አካባቢ በወረዳው ግራር ውሃ ቀበሌ ውስጥ ነው።

በዚህም የሰባት ህጻናት ህይወት ማለፉን አስታውቀዋል።

ከመተማ አብርሃጅራ ሲገነባ የነበረው የመንገድ ፕሮጀክት አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት መንገዱ  ሳይጠናቀቅ መቋረጡን አስታውሰዋል።

የመንገዱን ግንባታ ውል ወስዶ ሲሰራ የነበረው ሱር ኮንስትራክሽን ድርጅት መሆኑን አውስተው፤ ለመንገዱ ግንባታ አገልግሎት ሊውል የነበረ የድማሚት ፈንጅ በግራር ውሃ ቀበሌ ለፕሮጀክቱ በተሰራ ካምፕ ውስጥ በኮንቴነር ተከማችቶ እንደነበር  አመልክተዋል።

ካምፑ ምንም ዓይነት ጥበቃ እንደማይደረግለት የጠቀሱት ረዳት ኢንስፔክተር፤ ህፃናቱ በካምፑ ውስጥ ገብተው ሲጫወቱ የድማሚት ፈንጂውን ሲነካኩ ድንገት ፈንድቶ የሰዎች ህይወት ማለፈፉን ተናግረዋል።

አሁንም መሰል የድማሚት ቁስ በአካባቢው ተከማችቶ ስላለ የሚመለከተው አካል ፈጥኖ እንዲያነሳው  ረዳት ኢንስፔክተሩ  አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም