በአገራዊ የምክክር ሂደት ተግባቦትን በማሳለጥ በኩል የመገናኛ ብዙኃን የላቀ ሚና ይጠበቅባቸዋል

66

የካቲት 28/2014 ዓ/ም በአገራዊ የምክክር ሂደት ተግባቦትን በማሳለጥ በኩል የመገናኛ ብዙኃን የላቀ ሚና የሚጠበቅባቸው መሆኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ዮሐንስ ሽፈራው ገለጹ።

በርካታ የዓለም አገራት የውስጥ ፖለቲካዊ ቅራኔያቸውን ለመፍታት ብሔራዊ ምክክርን የመፍትሔ አማራጭ አድርገው እንደተጠቀሙበት መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ብሔራዊ የምክክር ሂደታቸውን በስኬት የቋጩ አገራት ለፖለቲካዊ አለመግባባት መነሻ የሆኑ ችግሮቻቸውን በጋራ በመፍታት በኢኮኖሚው ዘርፍ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።

ለአብነትም በአፍሪካ ሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ ስኬታማ ብሔራዊ ምክክር ማድረጋቸውን ተከትሎ የጋራ መግባባት የሰፈነበትና ብዝሃነትን የተቀበለ ሰላማዊ ሀገር እውን አድርገዋል፡፡

በዚህም የዜጎቻቸውን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማሳደግ በስኬት ከሚጠቀሱ ሀገራት መካከል ተቀምጠዋል።

ኢትዮጵያም በጥላቻ እየታጠረ የመጣውን ብሄር ዘመም የፖለቲካ አካሄድና አለመግባባት ዘለቄታዊ መፍትሄ ለማበጀት አገራዊ ምክክሩ ወሳኝ መሆኑን በርካቶች ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ዮሐንስ ሽፈራው፤ አገር አንድነቷን አስጠብቃ እንድትቀጥል መገናኛ ብዙኃን ጉልህ ሚና እንዳላቸው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኮሚሽን ተቋቁሞለት ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚካሄደው አገራዊ የምክክር ሂደት ስኬታማነት የመገናኛ ብዙኃን ተግባቦትን በማሳለጥ በኩል የላቀ ሚና ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የምክክር ሂደቱን በማሳለጥ ዜጎች ተግባቦት ፈጥረው በጋራ መንቀሳቀስ የሚያስችላቸውን አውድ ለማመቻቸት የመገናኛ ብዙኃኑ ሚና ጉልህ መሆኑን አንስተዋል።

ኢትዮጵያዊያንም የተሻለ የታሪክ አረዳድ በመያዝ፣ በመቻቻልና በምክንያታዊነት ላይ ለተመሰረተ ምክክር መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም