በጎንደር ከተማ ከ668ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለተጠቃሚው ማከፋፈል ሊጀመር ነው

116

ጎንደር ፤ የካቲት 28/2014 ዓ/ም በጎንደር ከተማ ገበያን ለማረጋጋት እንዲያግዝ ከ668ሺህ ሊትር በላይ የምግብ ዘይት በተያዘው ሳምንት ለተጠቃሚ ማከፋፈል እንደሚጀመር የከተማው ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ፡፡

የዘይት ምርትን በመደበቅ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት በሚፈጥሩ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች በከተማ አስተዳደሩ የተቋቋመው ግብር ሃይል እርምጃ መውሰድ መጀመሩም ተገልጿል፡፡

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ የዘይት ምርት ላይ የተፈጠረው የዋጋ ጭማሪ ከኢኮኖሚ አሻጥር ጋር የሚያያዝ ነው ያሉት ፡፡

በከተማው በግብርና ምርቶች ላይ ካለፈው ሃምሌ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ አለመኖሩን ጠቁመው፤  በምግብ ዘይት ላይ የታየው ድንገተኛ የዋጋ ጭማሪ ግን  የተጋነነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከተማ አስተዳዳሩ ገበያውን ለማረጋጋት አለ በጅምላ በኩል የሚሰራጭ 668ሺህ ሊትር የምግብ ዘይት ወደ ከተማው ተጓዞ እየገባ መሆኑን አስታውቀዋል።

በከተማው በሚገኙ የጅምላና ችርቻሮ ነጋዴዎች አማካኝነት ባለ 20 ሊትር ዘይት በ1ሺ 654 ብር  እንደሁም ባለ 5 ሊትር በ425 ብር እና ባለ 3 ሊትር ደግሞ በ261 ብር ከ24 ሳንቲም ሂሳብ  ሽያጭ ለነዋሪዎች እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በከተማው የሚታየውን የኑሮ ውድነት ለመቀነስ በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ እንዲቻል 32 ሚሊዮን ብር ብድር መፍቀዱንም ይፋ አድርገዋል፡፡

ለመንግስት ሰራተኞችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የዳቦ ዱቄት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማሰራጨት በከተማው ለሚገኙ የዱቄት ፋብሪካዎች 2 ሺህ ኩንታል ስንዴ መቅረቡን አስረድተዋል፡፡

ግብረ ሃይሉ ያለአግባብ ምርቶችን በደበቁና ባከማቹ እንዲሁም ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የንግድ ሱቆችን ከማሸግ ጀምሮ ንግድ ፈቃድ እስከ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ  መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

የምግብ ዘይትን ጨምሮ መንግስት ከቀረጥ ነጻ ከውጭ  እንዲገቡ ፈቃድ በሰጣቸው የፍጆታ ምርቶች ላይ ተገቢውን የዋጋ ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ግዛቸው መኮንን ናቸው፡፡

በከተማው ከአራት ቀን በፊት በ690 ብር ይሸጥ የነበረ ባለ 5 ሊትር ዘይት በአሁኑ ወቅት እስከ 900 ብር ነጋዴው በመጠየቅ  ችግር እየፈጠረ  በመሆን መንግስት እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

በጽዳት ስራ የሚተዳደሩት ወይዘሮ ብርቱካን አያሌው በበኩላቸው፤ በወር ከሚከፈለኝ ሁለት ሺህ ብር ደመወዝ አንድ ሺህ ብር ዘይት ገዝቶ ለመጠቀም ከአቅሜ በላይ በመሆኑ ኑሮ መምራት ከባድ ሆኗል ሲሉ  ተናግረዋል፡፡

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች መንግስት በተመጣጣኝ ዋጋ ዘይት በማቅረብ ህዝቡ እየደረሰበት ያለውን የኑሮ ጫና ሊያቃልል እንደሚገባ ጠቁመው፤ ሰበብ እየፈለጉ ያልተገባ ዋጋ በሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይም የማያዳግም ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ነዋሪዎቹ አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም