ሴቶች የአገርን ሰላም በማስጠበቅ እና የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው

137

የካቲት 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሴቶች የአገርን ሰላም በማስጠበቅ እና የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ111ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ46ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን “እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርሃ ግብሮች አክብሯል፡፡

በመርሃ-ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ በየደረጃው ከሚገኙ ሴት አመራሮች እና ከ11ሩም ክፍለ ከተሞች ከተውጣጡ ሴቶች ተገኝተዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ እንደገለጹት፤ ሴቶች የአገርን ሰላም በማስጠበቅ እና የህዝቦችን አንድነት በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው።

ይህንንም በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል የሚሆን ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ በተቃጣ አገር የመበተን እና ሉአላዊነትን የመዳፈር ሂደት ውስጥ ሰላምና ክብር እንዲጠበቅ በማድረግ ሴቶች ግንባር ቀደም ሚና ተጫውተዋል ሲሉም ገልጸዋል።

በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የአገርን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ ሴቶች በጦር ሜዳ ከፊት እየመሩ ጀግንነታቸውን አሳይተዋል፤ ሌሎች እናቶችም ለመከላከያ ሰራዊት ደጀንነታቸውን በማሳየት እንዲሁም የአገር አለኝታ መሆናቸውን አስመስክረዋል።

ይህንን የይቻላል እና የአይበገሬነት መንፈስ በማጠናከር ለሌላ ውጤት እና ስኬት መትጋት እንደሚገባም ጠቁመዋል።

" የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ህፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሀና የሺንጉስ በበኩላቸው፤ የሴቶችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማጎልበትና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች መልካም ውጤቶች ታይተዋል።

የሴቶችን አቅም በመገንባት፣ መብታቸው እንዲከበር እና በማንኛውም አገራዊ ጉዳይ ላይ እኩል ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ አምራችና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉም ገልጸዋል።

በዚህም የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለመኛረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ውጤታማ እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ ሃላፊነት መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም