በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከቂም ፖለቲካ መታቀብ ይገባል - የመብት ተሟጋች ታማኝ በየነ

55
አዲስ አበባ  ነሀሴ 27/2010 በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የለውጥ ሂደት ተጠናክሮ ቀጣይነት እንዲኖረው መላው ሀዝብ በተለይም ወጣቱ ከቂም በቀልና ከእልህ እርምጃዎች ራሱን ማቀብ አንዳለበት የመበት ተሟጓቹ አርቲስት ታማኝ በየነ አሳሰበ። ትናንት ወደ አገሩ ለተመለሰው ታማኝ በየነ በሚሊኒየም አዳራሽ ዛሬ ደማቅ ይፋዊ አቀባበል ተደርጎለታል። በስነ-ስርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የአማራ ከልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ባለስልጣናትና በሺዎች የሚቆጠሩ የከተማው እና አካባቢው ነዋሪ ተገኝተዋል። በዚሁ ወቅት አርቲስት ታማኝ ባደረገው ንግግር በኢትዮጵያ በነበረው ስርዓት በደረሰባቸው የተለያየ የፍትህ ጥሰት ሳቢያ ያቄሙ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም ወጣቶች መኖራቸውን ጠቅሷል። ሆኖም እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ከቂምና በቀል ይልቅ ለመፃኢው የኢትዮጵያ ደማቅ ተስፋ በእጅጉ ለሚጠቅመው ይቅርታ ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው አሳስቧል። በተለይ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚወስዳቸው እርምጃዎች ለአገሪቱ የሚበጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንደሚጠበቅበትም አስገንዝቧል። ለኢትዮጵያና ህዝቦቿ መጠናከር የሚበጀው አንድነት በመሆኑ መላው ህዝብ በብሄርና በማንነት ላይ ከታጠረ አስተሳሰብ እራሱን ማራቅ ይኖርበታል ሲልም አርቲሰት ታማኝ መክሯል። መነጣጠል ከጥቅሙ ይልቅ ጥፋቱ የከፋ መሆኑን ያሳሰበው አርቲስት ታማኝ ፍትህ፣ ነጻነትና እኩልነት የሰፈነባትን ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የሚበጀው አንድነት ነው ብሏል። አርቲስት ታማኝ በዚሁ ንግግሩ  በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ለተጀመረው ለውጥ " ከራሳቸው ህይወት ይልቅ ኢትዮጵያን ላስቀደሙ" ኢትዮጵያዊያን ያለውን አክብሮትም ገልጿል። በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ላይ የተለያዩ አካላትን የወከሉ አካለት ባስተላለፉት መልዕክትም ታማኝ ላለፉት 22 ዓመታት በኢትዮጵያ ፍትህና አኩልነት እንዲመጣ ላደረገው ትግል አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም