ምሁራን አገራዊ ምክክሩን አስመልክቶ የሚንሸራሸሩ ሀሳቦች የተገሩ እንዲሆኑ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው

92

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ምሁራን አገራዊ ምክክሩን አስመልክቶ የሚንሸራሸሩ ሀሳቦች የተገሩ እንዲሆኑ የማድረግ ሃላፊነት አለባቸው" ሲሉ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ አሳሰቡ።

ምሁራኑ በበኩላቸው አገራዊ ምክክሩን ውጤታማ ለማድረግ ሕዝብ በባለቤትነት ሊመራው ይገባል ብለዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር "አካታች ብሔራዊ ምክክሩን ከማሳካት አንጻር የምሁራን ሚና" በሚል ርዕስ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በመድረኩ ለአገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የምሁራን ተሳትፎና ሙያዊ ድጋፍ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

ምክክሩን በተለያዩ አካላት የሚንሸራሸሩ ሀሳቦች የተገሩ እንዲሆኑ የማድረግና ሳይንሳዊ ምልከታዎችን በማከል ሀሳቦችን ማላቅ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ምሁራን ጫፍ የረገጡ ሀሳቦች ወደ መሐል እንዲመጡ የሚያደርጉ ሞጋች ሀሳቦችን ማቅረብ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አለማየሁ ደበበ በበኩላቸው በአገራዊ ምክክሩ ጉዳይ የምሁራን ሚና "የጥሪ ተሳትፎ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ" መሆኑን ተናግረዋል።

አገራዊ ምክክሩ ሁሉም አሸናፊ የሚያደርግ ውጤት እንዲያመጣ የሚካሄዱ ውይይቶች ሁሉን አሳታፊና ሕዝብ በባለቤትነት ሊመራ ይገባል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዶክተር ባዩልኝ ዘመድአገኘሁ እንዳሉትም፤ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት በተለይም የምሁራን ሚና አይነተኛ ድርሻ ቁልፍ መሆኑንና ምክክሩን በጥናትና ምርምር ሥራዎች በመደገፍ እንዲሁም በውይይቱ ላይ የጎላ ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጸዋል።

አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቋቁሞና 11 ኮሚሽነሮች ተሰይመውለት በኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍና አሳታፊ ምክክር ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ የኮሚሽኑ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በቅርቡ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም