የመጽሀፍ ዋጋ መናርና መጻህፍትን እንደልብ አለማግኘት የንባብ ባህል እንዳይጎለብት እንቅፋት ሆናል

84

ዲላ (ኢዜአ) የካቲት 25/2014 የመጽሀፍ ዋጋ እየናረ መምጣትና መጻህፍትን እንደልብ አለማግኘት የንባብ ባህል እንዳይጎለብት እንቅፋት መሆናቸውን በዲለ ከተማ በተካሄደ የንባብ ሳምንት ላይ የተሳተፉ የህብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።
በቅርቡ በዲላ ከተማ በተካሄደው የንባብ ሳምንት ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች፣ እንዳሉት የንባብ ባህል እንዲዳብር በመጻህፍት አቅርቦት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል።

ከአስተያየታ ሰጪዎቹ መካከል በዲላ ከተማ የስነ አዕምሮ ባለሙያ ወጣት ሰመሃር አብዲ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷ ጀምሮ በወር ሁለት መጻህፍትን የማንበብ ልማድ እንደነበራት ገልጻለች።

በአሁኑ ወቅት የመጻህፍት ዋጋ ከዚህ ቀደም ከነበረው በመቶ እና በመቶ ሃምሳ ብር መጨመሩ ለንባብ እንቅፋት መሆኑን ተናገራለች።

ከወቅቱ ጋር አብረው የሚሄዱ የተለያዩ ይዘት ያላቸው መጻህፍት ከንባብ ቤቶች በሚፈለገው ደረጃ አለማግኘት ሌላው የዘርፉ ፈተና መሆኑንና የእሷንም የማንባብ ልማድ እየተፈታተነው መሆኑን ገልጻለች።

ንባብ ለአዕምሮ ጤንነትና ስብዕና ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ጠቁማ፣ እየተዳከመ የመጣው የንባብ ባህል እንዲያንሰራራ በመጻህፍት አቅርቦት ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አመልክታለች።

"በተለይ ትምህርት ቤቶችንና የህዝብ ቤተ መጻህፍትን የተለያየ ይዘት ባላቸው መጻህፍት ከማደራጀት ባለፈ፣ መጽሀፍ በቅናሽ ዋጋ ማግኘት የሚያስችሉ አውደ ርሂዮችን በከተሞች ማዘጋጀት ሊለመድ ይገባል" ብላለች።

ከትምህርትና ከማጣቀሻ መጻህፍት ውጭ የስነ ልቦና፣ የታሪክና የፍልስፍና መጽሀፎችን በቤተ መጻህፍት በሚፈለገው ልክ ለማግኘት እንደምትቸገር የተናገረችው ደግሞ በዲላ የደንቦስኮ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ መስታወት ትዕግስቱ ናት።

"የመጻህፍት ዋጋ የሚቀመስ አለመሆን በንባብ ልምዴ ላይ የራሱን ጫና ከማሳደሩ ባለፈ ዝንባሌዬን እንዳላዳብር ተጽኖ አሳድሯል" ትላለች።

ተማሪ መስታወት እንዳለችው በአሁኑ ወቅት ወጣቱ ትውልድ መጽሀፍ ከማንበብ ይልቅ ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ማዘውተርን ይመርጣል።

"ከዚህ ባለፈ ለመጤ ባህልና ጎጂ ድርጊቶች ተገዢ እየሆነ የመጣበት ሁኔታ በመኖሩ ትውልዱን ከዚህ በማላቀቅ ከንባብ ጋር የሚያቆራኙ ንቅናቄዎች ሊካሄዱ ይገባል" ብላለች።

በመጻህፍት ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ አባይነህ አድነው በበኩላቸው የመጽሀፍ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣት በሥራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ከመጻህፍት ጋር ያለው ቁርኝት እየቀነሰ መምጣት ለንባብ ባህል መቀነስ ተጨማሪ ምክንያት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

"የሚያነብ ትውልድ ለመፍጠር በተለይ ወጣቱ ሳይቸገር መጽሀፍ የሚያገኝበት አማራጭ ሊሰፋ ይገባል" ብለዋል።

"ማንበብ አንድን ሰው ሙሉ፣ ሞጋችና ምክንያታዊ እንዲሆን ያደርጋል" ያለው ደግሞ ደራሲ ዘነበ ወላ ነው።

በተለይ የነገ አገር ተረካቢ ወጣቱ ትውልድ በተለያዩ ነገሮች ሳይጠመድ ከትምህርትና ከንባብ በሚያገኛቸው የዕውቀት አማራጮች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ አሳስቧል።

የትውልዱ የንባብ ባህል እንዲዳብር የመጻህፍት አቅርቦትን በበቂ ደረጃ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ መክሯል።

በተለይ መንግስት በመጽሀፍ ግብዓቶች ላይ የዋጋ ቅናሽ እንዲኖር በመስራት የሚጽፉና የሚያሳትሙ ግለሰቦችና ተቋማት እንዲበራከቱ ማድረግ ይኖርበታል" ብሏል።

"አባቶቻችን ሳቢና አሳታፊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ባለቤት ቢሆኑም ይህን አንብቦ ካለመረዳት የተነሳ ትውልድ በትንሽ በትልቁ ሲነታረክ ይታያል" ያሉት ደግሞ በደቡብ ክልል ባህል ቱሪዝም ቢሮ የባህል አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ቡድን መሪ ወይዘሮ አብነት አዳነ ናቸው።

የንባብ ባህል እንዲዳብር ቢሮው በክልሉ የሚገኙ 43 ብሔር፣ ብሔርሰቦችን ባህል፣ ታሪክና ትውፊት በመጽሐፍ አሳትሞ እያሰራጨ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቅርቡ በዲላ ከተማ የተካሄደውን የንባብ ሳምንት ምክንያት በማድረግ ቢሮው ከ3 ሺህ በላይ የታሪክ፣ የባህልና የተለያዩ ይዘት ያላቸውን መጻህፍት ማሰራጨቱን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም