በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለማገዝና በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርበን ለመስራት ዝግጁ ነን--ኢዜማ

86

አዲስ አበባ የካቲት 25/2014 /ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለማገዝና በሌሎች የጋራ አገራዊ ጉዳዮች ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

የፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአፋር ክልል አሁንም እየፈጸመ ያለው ጥቃትና ወረራ፣ በሶማሌና ኦሮሚያ ክልል በድርቅ የተጎዱ ወገኖች ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ እንዲሁም የአሸባሪው ሸኔ ጥቃት በመግለጫው ከተነሱ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ኢዜማ አሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራ ተፈጽሞባቸው የነበሩ ክልሎች ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ የሚቃኝ ቡድን በማሰማራት መረጃ ማሰባሰቡን ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ በቅኝቱም አሸባሪ ቡድኑ የፈጸማቸውን ግፎችና ክልሎቹ ከቡድኑ ነጻ ከወጡ በኋላ ያሉበትን ሁኔታ ተመልክቷል ነው ያሉት፡፡

ፓርቲው መንግሥት በተለይም የዜጎች ዘላቂ ሰላምና ደኅንነት በማስጠበቅ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንዳለበት አሳስቧል።

ጎን ለጎንም አሸባሪው የሸኔ ቡድን በኦሮሚያ ክልል የሚፈጽማቸውን ወንጀሎች የመከላከል ሥራ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።  

ከዚህ አኳያ ፓርቲው ያሰባሰባቸውን መረጃዎች በመያዝ ከመንግስት ጋር ለመወያየት እንደሚፈልግም  ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪ ኢዜማ በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለማገዝና በሌሎች የጋራ አገራዊ ጉዳዮች ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ዋና ጸሐፊው አቶ አበበ አካሉ ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች ለተከሰተው ድርቅ ምላሽ ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ዝግጁ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው በኢትዮጵያ አሁን እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ኢዜማ የኢትዮጵያን ህዝብ በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ሁሌም በትብብር እንደሚሰራም ነው የገለጹት፡፡

መንግስት አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአፋር ክልል እየፈጸመ ያለውን ጥቃት ለማስቆም መስራት እንዳለበትም ፓርቲው ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም