ኅብረተሰቡ በየሦስት ወሩ በመደበኛነት ደም እንዲለግስ ጥሪ ቀረበ

75

አዲስ አበባ የካቲት 25/2014 /ኢዜአ/ ኅብረተሰቡ በየጊዜው የሚያጋጥመውን የደም እጥረት ለማቃለል በየሦስት ወሩ በመደበኛነት ደም እንዲለግስ ኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ።

በተቋሙ የደም ለጋሾች ዘርፍ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ተመስገን አበጀ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ደም ባንክ ያለው ክምችት ከዕለት ወደ ዕለት እየቀነሰ መጥቷል።

በዚህም ክምችቱ አሁን ከግማሽ በታች መድረሱን ገልጸው ለዚህም የደም ፈላጊዎች ቁጥር መጨመርና የደም ለጋሾች ቁጥር መቀነስ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን ነው ያስረዱት።

በተለይም በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በሐረሪና በአፋር ክልሎች የተስተዋለው የደም ፍላጎት መጨመር በአዲስ አበባ በሚገኘው የደም ባንክ ላይ ጫና መፍጠሩን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል "ኦ" የደመ አይነት ተፈላጊነቱ ከፍተኛ መሆንና ፕላትሌት የተባለው የደም አይነትም ተከማችቶ በባህሪው ብዙ አለመቆየቱም ለእጥረቱ ምክንያት ነው ብለዋል።    

በአዲስ አበባ የካንሰርና የደም የካንሰር ታካሚዎች እንዲሁም በወሊድ ምክንያት ደም የሚፈሳቸው እናቶች ቁጥር መጨመር፤ በደም ፍላጎትና በአቅርቦት መካከል ያለመመጣጠን ችግር እንዲኖር አስችሏል ብለዋል።

በዚህም ከዚህ ቀደም በቀን ይሰበሰብ ከነበረው ከ3 መቶ እስከ 4 መቶ ዩኒት ደም፤ አሁን ላይ ከ2 መቶ ዩኒት በታች እየተሰበ መሆኑን ነው የገለጹት።

ኅብረተሰቡም ደም መስጠት ሕይወት ማዳን መሆኑን ተገንዝቦ በየሦስት ወሩ ደም የመስጠት ባህሉን እንዲያጎለብት ጥሪ አቅርበዋል።

የደም ለጋሾች ቁጥር ለማሳደግ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም