በደሴ ጉዳት ለደረሰባቸው የትምህርት ተቋማት አንድ ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ

62

ደሴ የካቲት 25/2014(ኢዜአ) በደሴ ከተማ በአሸባሪው የህወሃት ቡድን የወደሙና የተዘረፉ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚያግዝ አንድ ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

ድጋፉን ያደረገው የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ  ምክትል ኃላፊ አቶ ደመላሽ ታደሰ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት፤ በሽብር ቡድኑ የወደሙ ተቋማትን በጋራ መለሶ ማቋቋም ከሁሉም እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

መምሪያው ወረዳዎችን በማስተባበር አንድ ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር  የሚገመት ቁሳቁስ አሰባስቦ አሸባሪው ቡድን በደሴ ጉዳት ላደረሰባቸው የትምህርት ተቋማት እንዲውል ድጋፉን ማምጣታቸውን ተናገረዋል፡፡

ከቁሳቁሶቹ መካከል ተቋማትን ስራ ማስጀመሪያ የሚሆን ኮምፒውተር፣ ፕሪንተርና የተለያዩ የጽህፈት መሳሪያዎች ይገኙበታል፡፡

አሸባሪው ህወሃት የበለጠ አንድነታችን እንዲጠናከር፣ እንድንተጋገዝና እንድንተባበር አድርጎናል ያሉት  አቶ ደመላሽ፤ ትምህርት ቤቶች መልሰው እንዲቋቋሙ የተጀመረው ድጋፍ  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቅር አበበ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ህወሃት ወረራ በፈጸመበት ወቅት 80 ትምህርት ቤቶችን መዝረፉንና ያልቻለውን ማውደሙን ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቶቹ መልሰው እንዲቋቋሙ ከባለድርሻ አካላት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው የወደሙትን በመጠገንና በማስተካከል ትምህርት እንዲጀምሩ ቢደረግም በቁሳቁስ እጥረት በሚፈለገው ልክ ማስተማር አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

መንግስት ህብረተሰቡንና ተቋሞችን በማስተባበር ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አመልክተውም፤ የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም